ዘፍጥረት 35:16-29
ዘፍጥረት 35:16-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ያዕቆብም ከቤቴል ተጓዘ፤ በጋዲር ግንብ አጠገብ ድንኳን ተከለ፤ ወደ ኤፍራታም ለመድረስ በቀረበ ጊዜ ራሔልን ምጥ ያዛት፤ በምጡም ተጨነቀች። በምጥ ሳለችም አዋላጂቱ፥ “አትፍሪ ይህኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንልሻልና” አለቻት። ከዚያም በኋላ ነፍስዋ ልትወጣ ደረሰች፤ ሞትዋ በእርሱ ሆኖአልና ስሙን የጭንቀቴ ልጅ ብላ ጠራችው ፤ አባቱ ግን ብንያም አለው። ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታም በምትወስድ መንገድ ተቀበረች፤ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት። ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፤ እርስዋም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ትባላለች። ከዚህም በኋላ እስራኤል በዚያች ምድር ሳለ ሮቤል ሄደ፤ ከአባቱ ከያዕቆብ ዕቅብት ከባላ ጋርም ተኛ፤ እስራኤልም ሰማ። በፊቱም ክፉ ነገር ሆነ። የያዕቆብም ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው፤ የልያ ልጆች፤ የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤ የራሔል ልጆች፤ ዮሴፍ፥ ብንያም፤ የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆችም፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤ የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆችም፤ ጋድ፥ አሴር፤ እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ፥ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት በአርባቅ ከተማ ወደምትገኘው ወደ መምሬ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ። የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ። ይስሐቅም ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተጨመረ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።
ዘፍጥረት 35:16-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ከቤቴል ተነሥተው ሄዱ፤ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፤ ምጡም ጠናባት። ምጡ አስጨንቋት ሳለ፣ አዋላጇ፣ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትገላገይ ነው” አለቻት። እርሷ ግን ሕይወቷ ልታልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች፣ ልጇን ቤንኦኒ አለችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው። ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተ ልሔም ተቀበረች። ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ሐውልት አቆመ፤ እስከ ዛሬም የራሔል መቃብር ምልክት ይኸው ሐውልት ነው። እስራኤልም ጕዞውን በመቀጠል ከጋዴር ወንዝ ባሻገር ድንኳኑን ተከለ። እስራኤልም በዚያ ምድር ሳለ፣ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋራ ተኛ፤ እስራኤልም ድርጊቱን ሰማ። ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም፦ የልያ ልጆች፦ የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፤ የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍ፣ ብንያም፤ የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች፦ ዳን፣ ንፍታሌም፤ የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆች፦ ጋድ፣ አሴር ናቸው። እነዚህ ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ወንዶች ልጆች ነበሩ። ያዕቆብ አባቱ ወዳለበት ወደ መምሬ መጣ፤ አብርሃምና ይሥሐቅ የኖሩባት፣ ቂርያት አርባቅ ወይም ኬብሮን የተባለችው ቦታ ናት። ይሥሐቅ መቶ ሰማንያ ዓመት ኖረ፤ ይሥሐቅም አርጅቶ፣ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹ ተሰበሰበ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።
ዘፍጥረት 35:16-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከቤቴልም ተነሡ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት በምጡም ተጨነቀች። ምጡም ባስጨነቅስት ጊዜ አዋላጂቱ፦ አትፍሪ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና አለቻት። እርስዋም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው አባቱ ግን ብንያም አለው። ራሔልልም ሞተች ወደ ኤፍራታ በምትወሰድም መንገድ ተቀበረች እርስዋም ቤተልሔም ናት። ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው። እስራኤልም ከዚያ ተነሣ ድንኳኑንም ከጋዴር ግንብ በስተ ወዲያ ተከለ። እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት እስራኤልም ሰማ። የያዕቆብም ልጆች አሥራ ሁለት ናቸው የልያ ልጆች የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤ የራሔል ልጆች ዮሴፍ፥ ብንይም፤ የራሔል ባርያ የባላ ልጆች፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤ የልያ ባሪያ የዘለፋ ልጆችም ጋድ አሴር እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ አብርሃምን ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት ወደ መምሬ ወደ ቂት ያትአርባቅ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ። የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠም፥ ሞተም ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።
ዘፍጥረት 35:16-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ያዕቆብና ቤተሰቡ ከቤትኤል ለቀው ሄዱ፤ ወደ ኤፍራታ ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው የራሔል መውለጃ ጊዜ ደረሰና በከባድ ምጥ ተያዘች። ምጧ እየበረታ በሄደ ጊዜ አዋላጅዋ “ራሔል ሆይ፥ ሌላ ወንድ ልጅ መውለድሽ ስለ ሆነ አይዞሽ አትፍሪ” አለቻት። እርስዋ ግን ልትሞት ታጣጥር ስለ ነበር ከመሞቷ በፊት ልጅዋን “ቤንኦኒ” አለችው፤ አባቱ ግን “ብንያም” አለው። ከዚህ በኋላ ወዲያውኑ ራሔል ሞተች፤ አሁን ቤተ ልሔም ተብሎ በሚጠራው ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ ዳር ተቀበረች። ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ለመታሰቢያዋ የሚሆን የድንጋይ ሐውልት አቆመ። ይህም ሐውልት እስከ ዛሬ ድረስ የራሔልን መቃብር ያመለክታል። ያዕቆብ ጒዞውን ቀጥሎ በዔዴር ግንብ ባሻገር ድንኳን ተክሎ ሰፈረ። ያዕቆብ በዚያ ምድር ሲኖር ሳለ፥ ሮቤል ወደ አባቱ ቁባት ወደ ባላ ገባ። ያዕቆብም ይህን ነገር ሰማ። የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው። የልያ ልጆች፥ የያዕቆብ የመጀመሪያ ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮርና ዛብሎን ናቸው። የራሔል ልጆች፥ ዮሴፍና ብንያም ናቸው። የራሔል አገልጋይ የነበረችው የባላ ልጆች፥ ዳንና ንፍታሌም ናቸው። የልያ አገልጋይ የነበረችው የዚልፋ ልጆች ጋድና አሴር ናቸው። እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በመስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ናቸው። ያዕቆብ በኬብሮን አጠገብ መምሬ ወደምትባል ስፍራ ወደሚኖረው አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄደ፤ ይህም ስፍራ አብርሃምና ይስሐቅ የኖሩበት ነው። ይስሐቅ መቶ ሰማኒያ ዓመት ኖረ፤ ዕድሜ ጠግቦ ካረጀ በኋላ ሞተ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።
ዘፍጥረት 35:16-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከቤቴልም ተነሡ፥ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፥ በምጡም ተጨነቀች። ምጡም ባስጨነቃት ጊዜ አዋላጂቱ፦ “አትፍሪ፥ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና” አለቻት። እርሷም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን “ቤንኦኒ” ብላ ጠራችው፥ አባቱ ግን ብንያም አለው። ራሔልም ሞተች፥ ወደ ኤፍራታ በምትወስድም መንገድ ተቀበረች፥ እርሷም ቤተልሔም ናት። ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፥ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው። እስራኤልም ከዚያ ተነሣ፥ ድንኳኑንም ከዔዴር ግንብ ባሻገር ተከለ። እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት፥ እስራኤልም ሰማ። የያዕቆብም ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው፥ የልያ ልጆች፥ የያዕቆብ በኩር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ የራሔል ልጆች፥ ዮሴፍና ብንያም ናቸው። የራሔል አገልጋይ የነበረችው የባላ ልጆች፥ ዳንና ንፍታሌም ናቸው። የልያ ባርያ የዚልፋ ልጆችም፥ ጋድ፥ አሴር ናቸው። እነዚህ በፓዳን-ኣሪም በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ መምሬ፥ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት፥ ወደ ቂርያት-አርባ፥ እርሷም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ። የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ። ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠ፥ ሞተም፥ ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፥ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።