ዘፍጥረት 35:16-29

ዘፍጥረት 35:16-29 NASV

ከዚያም ከቤቴል ተነሥተው ሄዱ፤ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፤ ምጡም ጠናባት። ምጡ አስጨንቋት ሳለ፣ አዋላጇ፣ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትገላገይ ነው” አለቻት። እርሷ ግን ሕይወቷ ልታልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች፣ ልጇን ቤንኦኒ አለችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው። ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተ ልሔም ተቀበረች። ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ሐውልት አቆመ፤ እስከ ዛሬም የራሔል መቃብር ምልክት ይኸው ሐውልት ነው። እስራኤልም ጕዞውን በመቀጠል ከጋዴር ወንዝ ባሻገር ድንኳኑን ተከለ። እስራኤልም በዚያ ምድር ሳለ፣ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋራ ተኛ፤ እስራኤልም ድርጊቱን ሰማ። ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም፦ የልያ ልጆች፦ የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፤ የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍ፣ ብንያም፤ የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች፦ ዳን፣ ንፍታሌም፤ የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆች፦ ጋድ፣ አሴር ናቸው። እነዚህ ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ወንዶች ልጆች ነበሩ። ያዕቆብ አባቱ ወዳለበት ወደ መምሬ መጣ፤ አብርሃምና ይሥሐቅ የኖሩባት፣ ቂርያት አርባቅ ወይም ኬብሮን የተባለችው ቦታ ናት። ይሥሐቅ መቶ ሰማንያ ዓመት ኖረ፤ ይሥሐቅም አርጅቶ፣ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹ ተሰበሰበ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}