ኦሪት ዘፍጥረት 35:16-29
ኦሪት ዘፍጥረት 35:16-29 አማ05
ያዕቆብና ቤተሰቡ ከቤትኤል ለቀው ሄዱ፤ ወደ ኤፍራታ ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው የራሔል መውለጃ ጊዜ ደረሰና በከባድ ምጥ ተያዘች። ምጧ እየበረታ በሄደ ጊዜ አዋላጅዋ “ራሔል ሆይ፥ ሌላ ወንድ ልጅ መውለድሽ ስለ ሆነ አይዞሽ አትፍሪ” አለቻት። እርስዋ ግን ልትሞት ታጣጥር ስለ ነበር ከመሞቷ በፊት ልጅዋን “ቤንኦኒ” አለችው፤ አባቱ ግን “ብንያም” አለው። ከዚህ በኋላ ወዲያውኑ ራሔል ሞተች፤ አሁን ቤተ ልሔም ተብሎ በሚጠራው ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ ዳር ተቀበረች። ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ለመታሰቢያዋ የሚሆን የድንጋይ ሐውልት አቆመ። ይህም ሐውልት እስከ ዛሬ ድረስ የራሔልን መቃብር ያመለክታል። ያዕቆብ ጒዞውን ቀጥሎ በዔዴር ግንብ ባሻገር ድንኳን ተክሎ ሰፈረ። ያዕቆብ በዚያ ምድር ሲኖር ሳለ፥ ሮቤል ወደ አባቱ ቁባት ወደ ባላ ገባ። ያዕቆብም ይህን ነገር ሰማ። የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው። የልያ ልጆች፥ የያዕቆብ የመጀመሪያ ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮርና ዛብሎን ናቸው። የራሔል ልጆች፥ ዮሴፍና ብንያም ናቸው። የራሔል አገልጋይ የነበረችው የባላ ልጆች፥ ዳንና ንፍታሌም ናቸው። የልያ አገልጋይ የነበረችው የዚልፋ ልጆች ጋድና አሴር ናቸው። እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በመስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ናቸው። ያዕቆብ በኬብሮን አጠገብ መምሬ ወደምትባል ስፍራ ወደሚኖረው አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄደ፤ ይህም ስፍራ አብርሃምና ይስሐቅ የኖሩበት ነው። ይስሐቅ መቶ ሰማኒያ ዓመት ኖረ፤ ዕድሜ ጠግቦ ካረጀ በኋላ ሞተ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።

