በዚያን ጊዜም የዳዊት አገልጋዮችና ኢዮአብ ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለ ሄደ፥ በኬብሮን አልነበረም። ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፥ “የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መጣ፥ አሰናበተውም እርሱም በሰላም ሄደ” ብለው ለኢዮአብ ነገሩት። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፤ “ምንድነው ያደረግከው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ፥ በሰላም እንዲሄድ ያሰናበትኸው ለምንድነው? የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ የመጣው ሊያታልልህ፥ መውጫና መግቢያህን ሊያውቅብህና፥ የምታደርገውን ሁሉ ሊሰልልህ ነው።” ከዚያም ኢዮአብ ከዳዊት ፊት እንደ ወጣ፤ ወደ አበኔር መልክተኞች ላከ፤ መልክተኞቹም ከሲራ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር። አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ፥ ኢዮአብ ለብቻው የሚያነጋግረው በመምሰል ወደ ቅጽሩ በር ይዞት ሄደ፤ እዚያም የወንድሙን የአሣሄልን ደም ለመበቀል ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው። ዳዊት ይህን ነገር ቆይቶ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በጌታ ፊት ለዘለዓለም ንጹሕ ነን፤ ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ከኢዮአብ ቤት ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም የሥጋ ደዌ ያለበት፥ በምርኲዝ የሚሄድ አንካሳ፥ ወይም በሰይፍ ተመቶ የሚሞት ወይም የሚበላው ያጣ ራብተኛ አይታጣ።” አበኔር ገባዖን ላይ በተደረገው ጦርነት የኢዮአብንና የአቢሳን ወንድም አሣሄልን ገድሎት ስለ ነበር፥ እነርሱም አበኔርን ገደሉት። ከዚያም ዳዊት ለኢዮአብና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ሁሉ፥ “ልብሳችሁን ቀዳችሁና ማቅ ለብሳችሁ በአበኔር ፊት አልቅሱ” አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ሄደ። አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም ጮኾ በአበኔር መቃብር ላይ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደዚሁ አለቀሱ። ንጉሡም ለአበኔር ይህን የኀዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤ “አበኔር እንደ ተራ ሰው ይሙት? እግሮችህ በእግር ብረት አልገቡም፤ ሰው በክፉ ሰዎች ፊት እንደሚወድቅ አንተም እንደዚሁ ወደቅህ።” ሕዝቡም ሁሉ እንደገና አለቀሱለት። ከዚያም ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ እንዲበላ አጥብቀው ለመኑት። ዳዊት ግን፥ “ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ያድርግብኝ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ማለ። ሕዝቡም ሁሉ ይህንኑ ተመልክተው ደስ አላቸው፤ በእርግጥ ንጉሡ ያደረገው ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሰኛቸው። በዚያን ዕለት ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል በሙሉ ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንዳልነበረበት ዐወቁ። ከዚያም ንጉሡ ለአገልጋዮቹ እንዲህ አለ፤ “በዛሬዪቱ ዕለት በእስራኤል መስፍንና ታላቅ ሰው መውደቁን አላወቃችሁምን? ምንም እንኳ ዛሬ የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም፥ እኔ ደካማ ሰው ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ ልጆች እጅግ በርትተውብኛል። ጌታ ለክፉ አድራጊ የእጁን ይስጠው።”
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3:22-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች