በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ለረጅም ጊዜ ቆየ፤ ሆኖም ዳዊት እያየለ ሲሄድ፥ የሳኦል ቤት ግን እየደከመ ነበር። ዳዊት በኬብሮን እያለ፥ ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ የበኲር ልጁ፥ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአሒኖዓም የተወለደው አምኖን፥ ሁለተኛው፥ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጌል የተወለደው ኪልአብ፥ ሦስተኛው፥ ተልማይ ከተባለው ከገሹር ንጉሥ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፥ አራተኛው፥ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤ አምስተኛው፥ ከአቢጣል የተወለደው ሸፋጥያ፥ ስድስተኛው፥ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረዓም ነበር፤ እነዚህ ዳዊት በኬብሮን እያለ የተወለዱለት ናቸው። የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ፥ አበኔር በሳኦል ቤት ሆኖ ኀይሉን ያጠናክር ነበር። ሳኦልም ሪጽፋን የምትባለውን የአያን ልጅ በዕቁባትነት አስቀምጦአት ነበር፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፥ “ለምንድን ነው ከአባቴ ዕቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው። ይህ የአበኔር ንግግር እጅግ ያስቆጣው ኢያቡስቴ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለአባትህ ለሳኦል ቤት፥ ለወንድሞቹና ለዘመዶቹ፥ ታማኝነቴን ሳላጎድል ይሄው አለሁ፤ አንተንም ለዳዊት እጅ አሳልፌ አልሰጠሁም፥ ዛሬ ግን አንተ በዚህች ሴት ትከሰኛለህን? በውኑ እኔ የውሻ ራስ ነኝ? ጌታ ለዳዊት በመሐላ የሰጠውን ተስፋ ከፍጻሜ ሳላደርስ ብቀር እግዚአብሔር በአበኔር ላይ ይፍረድ፤ ከዚያ የባሰም ያምጣበት፤ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ላይ የዳዊትን ዙፋን ለመመሥረት መንግሥትን ከሳኦል ቤት እንደሚወስድ ተስፋ ተሰጥቶታልና።” ኢያቡስቴም አበኔርን ስለ ፈራ ሌላ ቃል ሊመልስለት አልደፈረም። ከዚያም አበኔር ለዳዊት እንዲህ ሲሉ ለዳዊት እንዲነግሩት መልክተኞች ላከ፥ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እጄም ከአንተ ጋር ትሆናለች፥ እስራኤልንም ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ።” ዳዊትም፥ “ይሁን፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፥ ነገር ግን አንድ ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ፊቴን ለማየት በመጣህ ጊዜ፥ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህልኝ ፊቴን አታይም” አለ። ከዚያም ዳዊት፥ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት። ኢያቡስቴም መልክተኛ ልኮ፥ ሜልኮልን ከባሏ ከላይሽ ልጅ ከፓልጢኤል ወሰዳት። ባሏም እስከ ባሑሪም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፥ “ሂድ፥ ተመለስ” አለው፤ እርሱም ተመለሰ። አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ተመካከረ፥ “ቀደም ሲል ዳዊት ንጉሣችሁ እንዲሆን ፈልጋችሁ ነበር፤ ስለዚህ ጌታ ለዳዊት፥ ‘በአገልጋዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፥ ይህን አሁን አድርጉ።” እንዲሁም አበኔር ሄዶ ይህንኑ ለብንያማውያን ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ። አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋር ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን በመጣ ጊዜ፤ ዳዊት ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። ከዚያም አበኔር ዳዊትን፥ “ለጌታዬ ለንጉሡ መላውን እስራኤልን ልሰብስብ፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፥ ልብህ እንደተመኘውም ሁሉን እንድትገዛ ፈጥኜ ልሂድ” አለው። ስለዚህ ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ።
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos