በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ ጌታ ግን ደገፈኝ። ሰፊ ወደ ሆነ ስፍራ አወጣኝ፤ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ። ጌታ እንደጽድቄ መለሰልኝ፤ እንደ እጄም ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ፤ የጌታን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ ከአምላኬ ክፋት በማድረግ አልተለየሁም። ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ከሥርዓቱም አልራቅሁም። በፊቱ ያለ ነውር ነበርሁ፤ ራሴንም ከኃጢአት ጠብቄአለሁ። ጌታም እንደጽድቄ፥ በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ። “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ፥ ለቅን ሰው አንተም ቅን ሆነህ ትታያለህ። ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ ሆነህ ትታያለህ፥ ለጠማማ ሰው ግን ጠማማ ሆነህ ትታያለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህ፤ ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፥ ትዕቢተኞችን ይመለከታል። ጌታ ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤ ጌታም ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ርዳታ ሠራዊት አልፌ ወደ ፊት እሮጣለሁ፤ በአምላኬም ኃይል ቅጥሩን እዘላለሁ። የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የጌታም ቃል የጠራ ነው፤ ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤ ከጌታ በቀር አምላክ ማን ነው፤ ከአምላካችንስ በቀር ዓለት ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቀና እግዚአብሔር ነው። እግሮቼን እንደ ብሆር እግር ያበረታል፤ በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል። ክንዶቼም የናስ ቀስት መሳብ እንዲችሉ፥ እጆቼን ለጦርነት ያሰለጥናል። የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ምላሽህም ታላቅ አድርጎኛል። እርምጃዬን አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተሰነካከሉም። ጠላቶቼን አሳደድሁ፤ አጠፋኋቸውም፤ ሳላጠፋቸው ወደ ኋላ አልተመለስሁም። ፈጽሜ አጠፋኋቸው፤ አስጨነቅኻቸው ተመልሰውም እንዳይቆሙ፥ ከእግሬም ሥር ወድቀዋል። ለጦርነት ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፥ በላዬ የቆሙትን በበታቼ ታስገዛለህ። የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው። ለርዳታ ጮኹ፤ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ ጌታ ጮኹ፤ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም። በምድር ላይ እንዳለ ትቢያ አደቀቅዃቸው፤ በመንገድም ላይ እንዳለ ጭቃ ወቀጥኋቸው፤ ረገጥኋቸውም። ከሕዝቤ ጥቃት አዳንከኝ፤ የመንግሥታትም ራስ አደረግኸኝ፤ የማላውቀው ሕዝብ ተገዛልኝ፤ ባዕዳን ሊለማመጡኝ መጡ፤ እንደ ሰሙኝም በፍጥነት ይታዘዙኛል። ባዕዳን ፈሩ፤ ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ። ጌታ ሕያው ነው! ዐለቴ የተባረከ ይሁን፤ የመዳኔ ዓለት አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል። የሚበቀልልኝ አምላክ፥ ሕዝቦችን ከሥሬ የሚያስገዛልኝ፤ ከጠላቶቼ እጅ ነጻ የሚያወጣኝ እርሱ ነው። በጠላቶቼ ላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤ ከጨካኝ ሰዎችም እጅ ታደግኸኝ። ስለዚህ ጌታ ሆይ፥ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም ምስጋና እዘምራለሁ። ለንጉሡ ታላቅ ድል ይሰጠዋል፤ ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ፥ የማይለወጥ ፍቅሩን ያሳያል፥ ይህንንም ለዘለዓለም ያደርጋል።”
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22:19-51
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች