2 ሳሙኤል 22:19-51

2 ሳሙኤል 22:19-51 NASV

በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ። ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ። “እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤ እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም። ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም። በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤ ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፣ በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ። “ለታማኝ ሰው ታማኝ መሆንህን፣ ለፍጹም ሰው ፍጹም መሆንህን ታሳያለህ። ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣ ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ። አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤ ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፣ ትዕቢተኞችን ይመለከታል። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ጕልበት በሰራዊት ላይ እረማመዳለሁ፤ በአምላኬም ኀይል ቅጥር እዘላለሁ። “የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው፤ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻ ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ማን አምላክ አለ? ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው? ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣ መንገዴንም የሚያቀና እርሱ አምላኬ ነው። እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል። እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናቸዋል፤ ክንዶቼም የናስ ቀስት መገተር ይችላሉ። የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ድጋፍህ ታላቅ አድርጎኛል። ርምጃዬን አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተሰነካከሉም። “ጠላቶቼን አሳደድሁ፤ አጠፋኋቸውም፤ እስኪጠፉም ድረስ ወደ ኋላ አልተመለስሁም። ፈጽሜ አጠፋኋቸው፤ ተመልሰውም መቆም አልቻሉም፤ ከእግሬም ሥር ወድቀዋል። ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፣ ተቃዋሚዎቼንም ከእግሬ ሥር አንበረከክሃቸው። ጠላቶቼ ፊታቸውን አዙረው እንዲሸሹ አደረግሃቸው። ባላንጣዎቼንም ደመሰስኋቸው። ለርዳታ ጮኹ፤ የሚያስጥላቸው ግን አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም። በምድር ላይ እንዳለ ትቢያ አደቀቅኋቸው፤ በመንገድም ላይ እንዳለ ጭቃ ወቀጥኋቸው፤ ረገጥኋቸውም። “በሕዝቤ ከተቃጣብኝ አደጋ አዳንኸኝ፤ የመንግሥታትም ራስ አደረግኸኝ። የማላውቀውም ሕዝብ ተገዛልኝ፤ የባዕድ አገር ሰዎች ይፈሩኛል፤ እንደ ሰሙኝም ወዲያውኑ ይታዘዙኛል። ባዕዳን ፈሩ፤ ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ። “እግዚአብሔር ሕያው ነው! ዐለቴ የተባረከ ይሁን! አምላኬ የድነቴ ዐለት ከፍ ከፍ ይበል። በቀሌን የሚመልስልኝ፣ አሕዛብንም ከሥሬ የሚያስገዛልኝ እርሱ ነው፤ እርሱ ከጠላቶቼ እጅ ነጻ ያወጣኛል። አንተ ከጠላቶቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤ ከጨካኝ ሰዎችም እጅ ታደግኸኝ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ፤ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ስምህንም በመዝሙር እወድሳለሁ። “ለንጉሡ ታላቅ ድል ይሰጠዋል፤ ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ፣ ለዘላለም የማይለወጥ ፍቅሩን ያሳየዋል።”