ጌታ ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳኦልም እጅ በታደገው ጊዜ፥ ዳዊት የዚህን መዝሙር ቃል ለጌታ ዘመረ፤ እንዲህም አለ፤ ጌታ ዐለቴ ዐምባዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ የምደገፍበት፥ ዐለቴ፥ ጋሻዬና የመዳኔ ቀንድ ነው። እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፥ መጠጊያና አዳኜ ነው፤ አንተ ከጨካኞች ታድነኛለህ። ምስጋና የሚገባውን ጌታን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ሞገድ ከበበኝ፤ የጥፋትም ጐርፍ አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤ የሞትም ወጥመድ ተጋረጠብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፤ ወደ አምላኬም ጮኽሁ። እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም ከጆሮው ደረሰ። ምድርም ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤ የሰማያትም መሠረቶች ተናጉ፤ እርሱ ተቆጥቶአልና ራዱ። ከአፍንጫው የቁጣ ጢስ ወጣ፤ ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤ ከእርሱ የሚንበለበል ፍም ወጣ። ሰማያትን ሰንጥቆ ወደ ታች ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ። በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ ሲከንፍ ታየ። ሁለንተናውን በጨለማ ሰወረ፥ በውሃ በተሞላ ጥቅጥቅ ደመና፥ ራሱን ከበበ። በፊቱ ካለው ብርሃን የእሳት ፍም ነደደ። ጌታ ከሰማያት አንጐደጐደ፤ የልዑልም ድምፅ አስተጋባ። ፍላጻውን ሰደደ፤ በተናቸውም፤ በመብረቁም ብልጭታ አወካቸው። ከጌታ ተግሣጽ፥ ከአፍንጫው ከሚወጣው፥ ከእስትንፋሱ ቁጣ የተነሣ፥ የባሕር መተላለፊያዎች ታዩ፤ የምድር መሠረቶችም ተገለጡ። ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ። በርትተውብኝ ነበርና፥ ከብርቱ ጠላቶቼ፥ ከሚጠሉኝም ታደገኝ።
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች