ኢዮስያስም ለጌታ በኢየሩሳሌም ፋሲካን አከበረ፤ በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን መሥዋዕት አረዱ። ካህናቱንም በየሥርዓታቸው አቆመ፥ በጌታም ቤት እንዲያገለግሉ አጸናቸው። እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለጌታም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ፦ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን ጌታንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊትና ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፉት በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ራሳችሁን አዘጋጁ፤ እንደ ሕዝቡም እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶቻችሁ ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱ ለተከፋፈሉትም ለአባቶች ቤቶች ሌዋውያን ይኑሯቸው፤ ፋሲካውንም እረዱ፥ እናንተም ተቀደሱ፥ ጌታም በሙሴ አንደበት የተናገረውን ቃል እንዲያደርጉ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።” ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም በሬዎች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። መሳፍንቱም ለሕዝቡና ለካህናቱ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የጌታም ቤት አለቆች፥ ኬልቂያስ፥ ዘካርያስ፥ ይሒኤል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችና ፍየሎች፥ ሦስት መቶም በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ። የሌዋውያኑም አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤል፥ ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችና ፍየሎች፥ አምስት መቶም በሬዎች ለሌዋውያን ሰጡ። አገልግሎቱም በተዘጋጀ ጊዜ ካህናቱም በስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ። የፋሲካውንም መሥዋዕት አረዱ፥ ሌዋውያኑም ቁርበቱን ገፈፉ፥ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ። በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለጌታ እንዲያቀርቡ በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። የፋሲካውንም መሥዋዕት እንደ ሥርዓቱ በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቁርባን በምንቸትና በሰታቴ በድስትም ቀቀሉ፥ ለሕዝቡም ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሣፍም እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደነበረው እንደ ኤዶታም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ የደጁም ጠባቂዎች በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው እንዲርቁ አያስፈልጋቸውም ነበር።
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች