2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14

14
አሳ መንገሡ
1አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ ዐሥር ዓመት ያህል ዐረፈች። 2አሳም በአምላኩ በጌታ ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤ 3የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፥ ሐውልቶቹንም ሰባበረ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም#14፥3 የአሼራ ዓምዶችን። ቈረጠ፤ 4የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን እንዲሹ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲያደርጉ ይሁዳን አዘዘ። 5ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችና የዕጣን መሠዊያዎቹን አስወገደ፤ መንግሥቲቱም በእርሱ ሥር ሰላም የሰፈነባት ሆነች። 6ምድሪቱ ሰላም ሰፍኖባት ስለ ነበር በይሁዳ የተመሸጉትን ከተሞችን ሠራ፤ እንዲሁም ጌታ ዕረፍትን ሰጠጥቶት ስለ ነበር በዚያም ዘመን ጦርነት አልነበረበትም። 7ይሁዳንም እንዲህ አለ፦ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፥ ቅጥርና ግንብ፥ መዝጊያና መቀርቀሪያ እናድርግባቸው፤ አምላካችንን ጌታን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ አሁንም ድረስ የኛው ነች፤ እኛ ፈልገነዋል፥ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል።” እነርሱም ሠሩ ተከናወነላቸውም። 8ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ጋሻም የሚሸከሙ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ።
ኢትዮጵያ ያደረገችው ወረራ መገታቱ
9ኢትዮጵያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ። 10አሳም ሊጋጠመው ወጣ፥ በመሪሳም አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ። 11አሳም እንዲህ ብሎ ወደ አምላኩ ወደ ጌታ ጮኸ፦ “አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህምና፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ! በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ።” 12ጌታም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን ድል ነሣ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። 13አሳም ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፥ በጌታና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ የይሁዳ ሰዎችም እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰዱ። 14ከጌታም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ያዛቸው በጌራራ ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ ድል በማድረግ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዝበዛ ነበርና ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ። 15የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግም ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ማረኩ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ