ትንቢተ ዘካርያስ 10
10
ሕዝቡን ለመታደግ እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ
1እግዚአብሔር በበልግ ወራት ዝናብ እንዲሰጣችሁ ለምኑት፤ ዝናብ ያዘለ ደመናን የሚልክ እግዚአብሔር ነው፤ ዝናብንና የመስክ አትክልትን ለሁሉም የሚሰጥ እርሱ ነው። 2ጣዖቶች ዋጋቢስ ነገርን ይናገራሉ፤ ጠንቋዮችም ሐሰተኛ ራእይን ያያሉ፤ የማጭበርበሪያ ሕልምንም ይናገራሉ፤ ስለዚህ ሕዝቡ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ይባዝናሉ፤ ማጽናናታቸው ከንቱ ነው፤ ከንቱ የማጽናናት ቃል ይሰጣሉ።
3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኀይለኛ ቊጣዬ በሕዝቤ መሪዎች ላይ ይወርዳል፤ እኔ የሠራዊት አምላክ ለመንጋዬ ለይሁዳ ሕዝብ ስለምጠነቀቅ መሪዎቻቸውን እቀጣለሁ፤ የይሁዳንም ሕዝብ እንደ ኲሩ የጦር ፈረሴ አደርጋቸዋለሁ። 4ከይሁዳ ሕዝብ እንደ ማእዘን ድንጋይ፥ እንደ ድንኳን ካስማ፥ እንደ ጦርነት ቀስት ያሉ መሪዎችና የጦር አዛዦች ይወጣሉ። 5የይሁዳ ሕዝብ ጠላቶቻቸውን ረግጠው ከመንገድ ጭቃ ጋር እንደሚለውሱ እንደ ብርቱ ጦረኞች ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ስለ ሆነ በርትተው በመዋጋት ፈረሰኞችን ሳይቀር ድል ይነሣሉ።
6“እኔ የይሁዳን ሕዝብ ብርቱ አደርጋለሁ፤
የእስራኤልንም ሕዝብ እታደጋለሁ፤
ስለምራራላቸውም ሁሉንም ወደ አገራቸው እመልሳለሁ፤
ከዚህ በፊት ከቶ ጥዬአቸው እንደማላውቅ ይሆናሉ፤
እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ስለ ሆንኩ
ጸሎታቸውን እሰማለሁ።
7የእስራኤል ሕዝብ እንደ ብርቱ ጦረኞች ይሆናሉ፤
የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰውም ደስተኞች ይሆናሉ፤
ልጆቻቸውም ይህን ድል በማስታወስ ደስ ይላቸዋል፤
በእግዚአብሔርም ሐሤት ያደርጋሉ።
8“ሕዝቤን በጥቅሻ ጠርቼ
በአንድነት እሰበስባቸዋለሁ፤ እታደጋቸዋለሁም፤
ከዚህ በፊት እንደ ነበሩትም ቊጥራቸውን አበዛዋለሁ።
9በሕዝቦች መካከል ብበትናቸውም እንኳ፥
በሚኖሩባቸው ሩቅ አገሮች ሆነው ያስታውሱኛል፤
እነርሱና ልጆቻቸው ተርፈው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።
10ከግብጽ ምድር እመልሳቸዋለሁ፤
ከአሦር እሰበስባቸዋለሁ፤
ቦታ እስኪጠባቸው ድረስ በገለዓድና በሊባኖስም ጭምር አሰፍራቸዋለሁ።
11በመከራ ባሕር ውስጥ ሲያልፉ እኔ እግዚአብሔር
ማዕበሉን እመታለሁ፤
ጥልቅ የሆነውም የዓባይ ወንዝ ይደርቃል፤
ትዕቢተኛይቱ አሦር ትዋረዳለች፤
ግብጽም በትረ መንግሥትዋን ታጣለች።
12እኔ አምላካቸው አበረታቸዋለሁ
እነርሱም ለቃሌ ይታዘዛሉ።”
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997