ትንቢተ ዘካርያስ 11
11
የእምቢተኞች አወዳደቅ
1ሊባኖስ ሆይ!
እሳት ዛፎችሽን ያቃጥል ዘንድ
በሮችሽን ክፈቺ!
2የሊባኖስ ዛፎች ስለ ወደቁ፥ እናንተ የዝግባ ዛፎች
“ዋይ!” እያላችሁ አልቅሱ፤
ግርማ የነበራቸው ዛፎች ሁሉ ጠፍተዋል፤
ጥቅጥቅ ያለው ደን ስለ ተቈረጠ የባሳን ወርካዎች
“ዋይ!” እያላችሁ አልቅሱ።
3እረኞች ለምለም የሆነ መሰማሪያቸው ስለ ወደመ
“ዋይ!” እያሉ ሲያለቅሱ ስሙ፤
የዮርዳኖስን ወንዝ ተከትሎ ያለው
የደን መኖሪያቸው ስለ ተደመሰሰ፥
አንበሶች በሐዘን ሲያገሡ ስሙ።
ሁለቱ እረኞች
4እግዚአብሔር አምላኬ እንዲህ ብሎኛል፦ “እስቲ ለዕርድ የተዘጋጁትን የበግ መንጋ አሰማራ። 5የገዙአቸው ሰዎች በጎቹን በማረዳቸው አይቀጡበትም፤ የሸጡአቸውም ሰዎች ‘እግዚአብሔር ይመስገን በልጽገናል’ ይላሉ፤ እረኞቻቸው እንኳ ለእነርሱ አይራሩላቸውም።”
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔም ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖር ለማንም ሰው ርኅራኄ አላደርግም፤ እኔ ራሴ እያንዳንዱን ሰው ለጐረቤቱና ለንጉሡ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ምድሪቱን ያጠፋሉ፤ እኔም ከእነርሱ እጅ አልታደጋቸውም።”
7በጎቹን ይገዙና ይሸጡ ለነበሩት ሰዎች ተቀጥሬ እንዲታረዱ ለተፈረደባቸው የበጎች መንጋ እረኛ ሆንኩ፤ መንጋውንም በማሰማራበት ጊዜ ሁለት በትሮችን ወሰድኩ፤ አንደኛውን በትር “ተወዳጅ” ብዬ ጠራሁት፤ ሌላውን በትር “አንድነት” ብዬ ጠራሁት። 8ሦስቱ እረኞች እኔን ስላስቈጡኝና ስለ ጠሉኝ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አስወገድኳቸው። 9ከዚህ በኋላ መንጋውን እንዲህ አልኩ፦ “እኔ ከእንግዲህ ወዲህ እረኛችሁ አልሆንም፤ የሚሞቱት ይሙቱ፤ የሚጠፉትም ይጥፉ፤ የተረፉትም እርስ በርሳቸው ተባልተው ይለቁ፤” 10ቀጥሎም “ተወዳጅ” የተባለውን በትሬን አንሥቼ ሰበርኩት፤ ይህን ማድረጌም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ቃል ኪዳን መቋረጡን ለማመልከት ነው። 11በዚህ ዐይነት ቃል ኪዳኑ በዚያኑ ዕለት ፈረሰ፤ ይህንንም ሳደርግ ይመለከቱኝ የነበሩት የበግ ነጋዴዎች የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ዐወቁ። 12እኔም “ብትፈቅዱ ደመወዜን ስጡኝ፤ ባትፈቅዱ ተዉት” አልኳቸው፤ እነርሱም የአገልግሎቴን ዋጋ ሠላሳ ብር ሰጡኝ። #ማቴ. 26፥15።
13እግዚአብሔርም “በቤተ መቅደስ የገንዘብ መቀበያ ሣጥን ውስጥ ጣለው” አለኝ። ስለዚህም ለእኔ “በቂ ደመወዝ ነው” ብለው የሰጡኝን ሠላሳ ብር ወስጄ በሸክላ ሠሪው ገንቦ ውስጥ ጣልኩት። #ማቴ. 27፥9-10። 14ከዚህ በኋላ “አንድነት” የተባለውን ሁለተኛውን በትር ሰበርኩት፤ ይህንንም ማድረጌ በይሁዳና በእስራኤል መካከል የነበረው ወንድማማችነት መጥፋቱን ለማመልከት ነበር።
15ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “አሁንም እንደገና ራስህን እንደ ዋጋቢስ እረኛ አድርግ፤ 16እነሆ በምድሪቱ መንጋዬን የሚጠብቅ አንድ እረኛ አስነሣለሁ፤ ይህን በማድረግ ፈንታ እርሱ ስለ ጠፉት አያስብም፤ የባዘኑትን አይፈልግም፤ ያነከሱትን አይፈውስም፤ ጤናማዎችንም አይመግብም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ የወፈረውን እያረደ ይበላል፤ ሰኮናቸውንም ይቈራርጣል። 17መንጋውን ለከዳ ለእንዲህ ዐይነቱ ዋጋቢስ እረኛ ወዮለት! ክንዱና ቀኝ ዐይኑ በሰይፍ ይመታ፤ ክንዱ በፍጹም ይድረቅ፤ ቀኝ ዐይኑም ጨርሶ ይጥፋ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997