የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 12

12
የኢየሩሳሌም የመዳን ተስፋ
1ሰማይን የዘረጋ፥ ምድርን የመሠረተ፥ ለሰውም የሕይወትን እስትንፋስ የሰጠ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል እንዲህ ይላል፦ 2“ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉ ሕዝቦች ጠጥተውት እንደሚያንገዳግድ የወይን ጠጅ ዋንጫ አደርጋታለሁ፤ እነርሱ ኢየሩሳሌምን በሚይዙ ጊዜ የቀሩትም የይሁዳ ከተሞች ይከበባሉ። 3በዚያን ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ እንደ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ እርስዋን ለማንሣት የሚሞክር ሁሉ ራሱን ይጐዳል፤ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እርስዋን ለማጥቃት ተባብረው ይመጣሉ፤ 4በዚያን ጊዜ ፈረሶቻቸውን በፍርሃት አስጨንቃለሁ፤ ፈረሰኞችንም አሳብዳለሁ፤ የጠላቶቻቸውን ፈረሶች አሳውራለሁ፤ የይሁዳን ሕዝብ ግን በዐይኔ እየተመለከትኩ እጠብቃቸዋለሁ። 5በዚያን ጊዜ የይሁዳ አለቆች በልባቸው ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አምላካቸው ስለ ሆነ በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ሕዝቡ በእርሱ ኀይልን ያገኛሉ’ ይላሉ።
6“በዚያን ጊዜ የይሁዳን ሕዝብ አለቆች በእሳት ማንደጃ ላይ ተከምሮ እንደሚነድ እንጨት፥ በእህል ነዶዎች መካከል እንደ ተቀጣጠለ ችቦ አደርጋቸዋለሁ፤ በአካባቢው ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ያወድማሉ፤ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ግን ምንም ሳይደርስባቸው በከተማይቱ ውስጥ ይኖራሉ።
7“እኔ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ለይሁዳ ነገድ ድልን አጐናጽፋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው የዳዊት ልጆች ክብርና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ክብር ከሌሎቹ የይሁዳ ነገድ ተወላጆች ከፍ ከፍ እንዳይል ነው። 8በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንደ ጋሻ መከታ እሆንላቸዋለሁ፤ ከእነርሱ እጅግ ደካማ የተባለው እንኳ የዳዊትን ያኽል ብርቱ ይሆናል፤ የዳዊት ልጆች እንደ እኔ እንደ እግዚአብሔር ወይም እንደ መላእክት ሆነው ሕዝቡን ይመራሉ። 9በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ላይ በጠላትነት የሚነሡትን የአሕዛብ መንግሥታት ሁሉ ለመደምሰስ እነሣለሁ።
10“በዚያን ጊዜ በዳዊት ዘሮችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የርኅራኄና የጸሎት መንፈስ እሞላለሁ፤ ይህንንም የማደርገው እነርሱ ለአንድያ ልጅና ለበኲር ልጅ እንደሚለቀስ ለወጉት ምርር ብለው እንዲያለቅሱለት ነው። #ዮሐ. 19፥37፤ ራዕ. 1፥7። 11በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም የሚሰማው ለቅሶ በመጊዶ ሜዳ ለሀዳድሪሞን እንደ ተለቀሰለት ለቅሶ ይሆናል። 12በምድሪቱ ላይ የእያንዳንዱ ወገን ቤተሰብ ለየራሱ ያለቅሳል፤ ሚስቶቻቸውም ለየራሳቸው ያለቅሳሉ፤ በዚህ ዐይነት የዳዊት ቤተሰብ ከነሚስቶቻቸው፥ የናታን ቤተሰብ ከነሚስቶቻቸው፥ 13የሌዊ ቤተሰብ ከነሚስቶቻቸው፥ የሺምዒ ቤተሰብ ከነሚስቶቻቸው፥ በየወገናቸው ሆነው ያለቅሳሉ፤ 14የቀሩትም በቤተሰቦች ተከፋፍለው ያለቅሳሉ፤ ሚስቶቻቸውም ለብቻ ተለይተው በማዘን ያለቅሳሉ።” #ማቴ. 24፥30፤ ራዕ. 1፥17።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ