ትንቢተ ዘካርያስ 9
9
ጐረቤት በሆኑ በእስራኤል ጠላቶች ላይ የሚመጣ ፍርድ
1የሰዎችና የእስራኤል ነገዶች ዐይኖች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ይመለከታሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በሐድራክና በደማስቆ ከተሞች ላይ ይፈርዳል። #ኢሳ. 17፥1-3፤ ኤር. 49፥23-27፤ አሞጽ 1፥3-5። 2ይህም የፍርድ ቃል የሐድራክ አዋሳኝ በሆነችው ሐማትና፥ ብዙ ጥበብ ባላቸው በጢሮስና በሲዶና ከተሞችም ይደርስባቸዋል። 3ጢሮስ ለራስዋ መጠበቂያ ብዙ ምሽጎችን ሠርታለች፤ ብዛቱ እንደ ትቢያና እንደ ዐፈር የበዛ ብርና ወርቅ አከማችታለች። 4ነገር ግን የሰበሰበችውን ሁሉ እግዚአብሔር ይወስድባታል፤ ሀብትዋን ወደ ባሕር ይጥለዋል፤ ከተማይቱም በእሳት ተቃጥላ ዐመድ ትሆናለች። #ኢሳ. 23፥1-18፤ ሕዝ. 26፥1—28፥26፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥9-10፤ ማቴ. 11፥21-22፤ ሉቃ. 10፥13-14።
5የአስቀሎና ከተማ ይህን አይታ ትፈራለች፤ የጋዛ ከተማም ይህን በማየት እጅግ ትጨነቃለች፤ ዔቅሮንም እንዲሁ ተስፋ ትቈርጣለች፤ ጋዛ ንጉሥዋን ታጣለች፤ አስቀሎናም ምድረ በዳ ሆና ትቀራለች። #ኢሳ. 14፥29-31፤ ኤር. 47፥1-7፤ ሕዝ. 25፥15-17፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥6-8፤ ሶፎ. 2፥4-7። 6በአሽዶድ ድብልቅ ሕዝብ ይኖራል፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነዚህን ትዕቢተኞች ፍልስጥኤማውያንን አዋርዳቸዋለሁ፤ 7ከእንግዲህ ወዲህ ደም ያለበትን ጥሬ ሥጋ ወይም ማንኛውንም የተከለከለ ምግብ አይበሉም፤ ከእነርሱ የተረፉት ከሕዝቤ ተቀላቅለው ከይሁዳ ነገድ እንደ አንድ ጐሣ ይሆናሉ፤ የዔቅሮን ሕዝብ ልክ እንደ ኢያቡሳውያን ከሕዝቡ ጋር ይቀላቀላሉ። 8ከዚህ በኋላ ምድሬን ዙሪያዋን ከብቤ እጠብቃለሁ፤ የወራሪ ኀይል መተላለፊያም አላደርጋትም። ሕዝቤ ምን ያኽል እንደ ተሠቃየ ስለ ተመለከትኩ ከእንግዲህ ወዲህ ጨቋኞች አይወሩአቸውም።”
የሚመጣው የጽዮን ንጉሥ
9ጽዮን ሆይ! ደስ ይበልሽ!
ኢየሩሳሌም ሆይ! በደስታ እልል በይ!
እነሆ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፥
በአህያይቱ ማለትም በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ፥
በድል አድራጊነት ወደ አንቺ ይመጣል። #ማቴ. 21፥5፤ ዮሐ. 12፥15።
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እኔ ሠረገሎችን ከእስራኤል፥
የጦር ፈረሶችንም ከኢየሩሳሌም አስወግዳለሁ፤
የጦር ቀስቶችን እሰባብራለሁ፤
ንጉሥሽ በሕዝቦች መካከል
ሰላም እንዲኖር ያደርጋል፤
ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕርና
ከታላቁ ወንዝ ጀምሮ
እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይሆናል።” #መዝ. 72፥8።
የእግዚአብሔር ሕዝብ ተማርከው ከተወሰዱበት እንደሚመለሱ
11“በመሥዋዕት ደም ከአንቺ ጋር ቃል ኪዳን ስለ ገባሁ፥
ውሃ ከማይገኝበት ጒድጓድ እስረኞችሽን ነጻ አወጣለሁ። #ዘፀ. 24፥8።
12እናንተ የተስፋ ባለቤት የሆናችሁ ምርኮኞች ሆይ!
እኔ ዛሬ ቀድሞ ከነበራችሁ በእጥፍ ስለምሰጣችሁ፥
ወደ አምባችሁ ተመለሱ።
13ይሁዳን እንደ ቀስት፥
እስራኤልንም እንደ ተወርዋሪ ፍላጻ እጠቀምባታለሁ፤
የግሪክ አገርን ወንዶች ልጆች ለመውጋት፥
የጽዮንን ወንዶች ልጆች እንደ ሰይፍ አድርጌ እልካቸዋለሁ።”
14እግዚአብሔር ከሕዝቡ በላይ ይገለጣል፤
የእርሱም ፍላጻዎች እንደ መብረቅ ይወረወራሉ፤
እግዚአብሔር አምላክ የመለከት ድምፅ ያሰማል፤
ከደቡብ በኩል እንደሚመጣ ዐውሎ ነፋስ ያልፋል።
15የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይከላከልላቸዋል፤
እነርሱም ጠላቶቻቸውን ይደመስሳሉ፤ የጠላትንም የወንጭፍ ድንጋይ ይረጋግጣሉ፤
የወይን ጠጅ ጠጥቶ እንደ ሰከረ ሰው ይጮኻሉ፤
የጠላቶቻቸውም ደም የመሥዋዕት ደም በሳሕን ሞልቶ
በመሠዊያ ላይ እንደሚፈስስ ይፈስሳል።
16ያም ቀን ሲደርስ እረኛ በጎቹን ከአደጋ እንደሚያድን
አምላካቸው እግዚአብሔር ሕዝቡን ያድናል።
በዘውድ ላይ ያለ ጌጥ እንደሚያበራ፥
እነርሱም በእግዚአብሔር ምድር ያበራሉ።
17የምድሪቱም መልካምነትና ውበት ምንኛ አስደናቂ ይሆናል!
በእርስዋ የሚገኘው እህልና የወይን ጠጅ
ወጣት ወንዶችና ሴቶችን ያለመልማቸዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997