የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 8

8
ኢየሩሳሌምን ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ ለመመለስ እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ
1የሠራዊት አምላክ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“ለሕዝብዋ ስላለኝ ፍቅር ኢየሩሳሌምን መርዳት እፈልጋለሁ፤ በጠላቶችዋ ላይ እንድቈጣ ያደረገኝም ይኸው ስለ እርስዋ ያለኝ ፍቅር ነው። 3እኔ እንድኖርባት ወደ ተቀደሰችው ከተማዬ ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ የታመነች ከተማ በመሆን ትታወቃለች፤ እኔ የሠራዊት አምላክ የምኖርበት ተራራ፥ የተቀደሰ ተራራ ተብሎ ይጠራል፤ 4ሰዎች ረጅም ዕድሜ ስለሚኖሩ ሽማግሌዎችና አሮጊቶች ምርኲዝ እየያዙ በመሄድ በኢየሩሳሌም አደባባዮች እንደገና ይቀመጣሉ፤ 5መንገዶችዋም ሁሉ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንደገና የተሞሉ ይሆናሉ።
6“በእነዚህ ቀኖች ከሕዝቡ ለተረፉት ይህ የማይቻል ነገር ቢመስልም እንኳ በውኑ ለእኔ የማይቻል ነገር አለን? 7እኔ ሕዝቤን በስደት ከሚኖሩበት ከምሥራቅና ከምዕራብ አገር እታደጋቸዋለሁ፤ 8መልሼ በማምጣት በኢየሩሳሌም እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላካቸው እሆናለሁ።
9“ለሠራዊት አምላክ ቤተ መቅደስን እንደገና ለመሥራት መሠረት በተጣለበት በቅርብ ጊዜ የነበሩ ነቢያት የተናገሩትን ቃል የሰማችሁ እናንተ አይዞአችሁ በርቱ! 10ከእነዚያ ቀኖች በፊት ለሰዎች የድካም ዋጋ ለእንስሶችም ኪራይ አይከፈልም ነበር፤ ሰውን ሁሉ በጐረቤቱ ላይ በጠላትነት እንዲነሣሣ ስላደረግሁ ማንም ሰው ሲወጣና ሲገባ ሰላም አልነበረውም። 11አሁን ግን ከዚህ ሕዝብ የተረፉትን እንደ ቀድሞው ጊዜ አላደርግባቸውም። 12እህላቸውን በሰላም ዘርተው ፍሬውን ይሰበስባሉ የወይን ተክሎቻቸውም ያፈራሉ። በቂ ዝናብ ስለሚዘንብ ምድሪቱ ብዙ ሰብል ትሰጣለች፤ ከስደት ለተረፉት ሕዝብ ይህን ሁሉ በረከት እሰጣለሁ። 13በሕዝቦች ዘንድ እንደ ርግማን ትቈጠሩ የነበራችሁት እናንተ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች ሆይ! እኔ አድናችኋለሁ፤ ለበረከትም ትሆናላችሁ፤ ስለዚህ አትፍሩ! በርቱ።”
14“እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ባስቈጡኝ ጊዜ ባለመራራት ቅጣት ላመጣባችሁ ወሰንኩ። 15ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ሕዝብ መልካምን ነገር ማድረግ ወስኜአለሁና አይዞአችሁ፤ አትፍሩ። 16እናንተ ልታደርጉት የሚገባ ነገር ይህ ነው፦ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በፍርድ ሸንጎዎቻችሁ ሰላም የሚገኝበትን እውነተኛ ፍርድ ስጡ። #ኤፌ. 4፥25። 17እርስ በርሳችሁ ለመጐዳዳት አንዱ በሌላው ላይ ተንኰል አያስብ፤ በሐሰት አትማሉ፤ እኔ ይህን ሁሉ እጠላለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
18የሠራዊት አምላክ እንዲህ አለኝ፦ 19“በአራተኛው፥ በአምስተኛው፥ በሰባተኛውና በዐሥረኛው ወር ትጠብቁት የነበረው ጾም ሁሉ ለይሁዳ ሕዝብ የተድላና የደስታ በዓል ይሆንላቸዋል፤ እናንተ ግን እውነትንና ሰላምን ውደዱ።”
20የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ሌሎች ሕዝቦችና በብዙ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም የሚጐርፉበት ጊዜ ይመጣል። 21የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ከተማ ሄደው ‘ኑ! ከሠራዊት አምላክ ቸርነትን እንለምን፤ እኛም ወደዚያ መሄዳችን ነው!’ ይሉአቸዋል። 22በዚህ ዐይነት ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና የእርሱንም በረከት ያገኙ ዘንድ ለመጸለይ ብዙ ሰዎችና ታላላቅ ሕዝቦች ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ። 23በእነዚያ ቀኖች ዐሥር የሌላ አገር ሰዎች ወደ አንድ አይሁዳዊ ቀርበው የልብሱን ዘርፍ በመያዝ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለ ሰማን ከእናንተ ጋር እንሂድ’ ይሉታል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ