ትንቢተ ዘካርያስ 7
7
እግዚአብሔር ትክክለኛ ያልሆነውን ጾም አይቀበለውም
1ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ኪስሌው የተባለ ዘጠነኛው ወር በገባ በአራተኛው ቀን እግዚአብሔር ለዘካርያስ የነገረው ቃል ይህ ነው፤ 2የቤትኤል ነዋሪዎች ሣርኤጼርንና ሬጌሜሌክን አብረዋቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላኩአቸው፤ የላኩአቸውም የእግዚአብሔር በረከት ይወርድ ዘንድ እንዲጸልዩና፥ 3የቤተ መቅደሱን ካህናትና ነቢያትን “እስከ አሁን ለብዙ ዓመቶች እንዳደረግነው በየአምስተኛው ወር በመጾም ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ ማዘናችንን እንቀጥልን?” ብለው እንዲጠይቁ ነበር።
4ከዚህም በኋላ ወደ እኔ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ 5ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉና ለካህናቱ እንዲህ በላቸው፦ “ባለፉት ሰባ ዓመቶች በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር የጾማችሁትና ያዘናችሁት እኔን ለማክበር ነበርን? 6በምትበሉበትና በምትጠጡበትስ ጊዜ የምትበሉትና የምትጠጡት ለራሳችሁ ብቻ አልነበረምን?”
7ኢየሩሳሌም በልጽጋና በሕዝብ ተሞልታ በነበረችበት ጊዜ፥ በከተማይቱ ዙሪያ ባሉ መንደሮች ብቻ ሳይሆን በደቡብ ክፍልና በምዕራብ ኰረብቶች ግርጌ ብዙ ሕዝብ በሚኖሩበት ዘመን እግዚአብሔር በቀድሞ ነቢያቱ አማካይነት የተናገረውም ይህንኑ ቃል ነበር።
አለመታዘዝ የስደት ምክንያት መሆኑ
8እግዚአብሔር ዘካርያስን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 9“እኔ የሠራዊት አምላክ ለሕዝቤ የሰጠሁት ትእዛዝ ይህ ነበር፤ ‘በትክክል ፍረዱ፥ እርስ በርሳችሁም አንዳችሁ ለሌላው ምሕረትና ርኅራኄን አድርጉ፤ 10በመካከላችሁ የሚኖሩትን ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፥ አባትና እናት የሌላቸውን ድኻ አደጎች፥ መጻተኞችንና ችግረኞችን አትጨቊኑ፤ እርስ በርሳችሁ አንዳችሁ ሌላውን ለመጒዳት አታስቡ።’
11“እነርሱ ግን ላለማዳመጥ እልኸኞች ሆኑ፤ እንዳይሰሙም ጆሮአቸውን ደፈኑ። 12ልባቸውንም እንደ አለት ድንጋይ አጠነከሩ፤ ጥንት በነበሩት ነቢያት አማካይነት እኔ የሠራዊት አምላክ በመንፈሴ የሰጠኋቸውን ሕግ ሁሉ በእልኸኛነት የማያዳምጡ ሆኑ፤ ስለዚህ እኔ የሠራዊት አምላክ ኀይለኛ ቊጣ አወረድኩባቸው። 13እኔ ስናገር ‘አናዳምጥም’ ስላሉ፥ እነርሱም ወደ እኔ በጸለዩ ጊዜ መልስ አልሰጠኋቸውም ይላል የሠራዊት አምላክ። 14እንደ ዐውሎ ነፋስ ጠራርጌ በመውሰድም በማያውቁት ባዕድ አገር እንዲኖሩ አደረግኋቸው፤ ይህችም መልካም ምድር ማንም የማይኖርባት ባድማ ሆና ቀረች፥ ያቺ ያማረች ምድርም ባድማ ሆነች።”
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997