አራተኛው መልአክ ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ፀሐይም ሰዎችን በግለትዋ ለማቃጠል ኀይል ተሰጣት፤ ሰዎች በታላቅ ግለት ተቃጠሉ፤ በእነዚህ መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ንስሓ አልገቡም፤ እርሱንም አላከበሩም። አምስተኛው መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም መንግሥት ጨለማ ሆነ፤ ሰዎች ከሥቃያቸው የተነሣ ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር፤ ከሕመማቸውና ከቊስላቸው የተነሣ የሰማይን አምላክ ተራገሙ፤ ከሥራቸውም ንስሓ አልገቡም። ስድስተኛው መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ ለማዘጋጀት የወንዙ ውሃ ደረቀ። ከዘንዶው አፍና ከአውሬው አፍ፥ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ። እነርሱ ተአምራት የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው፤ እነዚህ መናፍስት ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት ሰዎችን ለመሰብሰብ ወደ ዓለም ነገሥታት ሁሉ ይሄዳሉ። “እነሆ! እኔ እንደ ሌባ በድንገት እመጣለሁ! ራቁቱን እንዳይሆንና ኀፍረቱን ሰዎች እንዳያዩበት ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው የተመሰገነ ነው!” መናፍስቱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቡአቸው። ሰባተኛው መልአክ ጽዋውን በዐየር ላይ አፈሰሰ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካለው ዙፋን “ተፈጸመ!” የሚል ከፍተኛ ድምፅ ወጣ። መብረቅ፥ ድምፅ፥ ነጐድጓድና ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ይህን የመሰለ ታላቅ የምድር መናወጥ ሰው በምድር ላይ ከተፈጠረ ጀምሮ ሆኖ አያውቅም። ታላቂቱ ከተማ ከሦስት ተከፈለች፤ የአሕዛብ ከተሞችም ፈራረሱ፤ እግዚአብሔር ታላቂቱን ባቢሎንን አስታወሰ፤ የብርቱ ቊጣው ወይን ጠጅ የተሞላበትን ጽዋ እንድትጠጣም አደረጋት። ደሴቶች ሁሉ ወዲያ ሸሹ፤ ተራራዎችም አልተገኙም፤ እያንዳንዱ አርባ አምስት ኪሎ ግራም ያኽል የሚመዝን በረዶ ከሰማይ በሰዎች ላይ ወረደ፤ መቅሠፍቱ እጅግ አሠቃቂ ስለ ነበረ ሰዎች በበረዶው መቅሠፍት ምክንያት እግዚአብሔርን ተሳደቡ።
የዮሐንስ ራእይ 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 16:8-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች