የዮሐንስ ራእይ 16
16
የእግዚአብሔርን ቊጣ የያዙ ጽዋዎች
1ከዚህ በኋላ ሰባቱን መላእክት “ሂዱ! የእግዚአብሔርን ቊጣ የያዙትን ሰባቱን ጽዋዎች በምድር ላይ አፍስሱ!” የሚል ከፍ ያለ ድምፅ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ሰማሁ።
2የመጀመሪያው መልአክ ሄደና ጽዋውን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬው ምልክት ባለባቸውና ለአውሬው ምስል በሚሰግዱ ሰዎች ላይ መጥፎና የሚያሠቃይ ቊስል ወጣባቸው። #ዘፀ. 9፥10።
3ሁለተኛው መልአክ ጽዋውን በባሕር ላይ አፈሰሰ፤ ባሕሩም እንደ ሞተ ሰው ደም ሆነ፤ በባሕሩ ይኖሩ የነበሩት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ሞቱ።
4ሦስተኛው መልአክ ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ላይ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ፤ 5በውሃ ላይ ሥልጣን ያለው መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ያለህና የነበርክ ቅዱስ ጌታ ሆይ! እንዲህ ስለ ፈረድክ አንተ ትክክለኛ ነህ፤ 6ሰዎች የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደም አጠጣሃቸው፤ ይህም የሚገባቸው ነው፤” 7በመሠዊያውም “አዎ! ሁሉን የምትችል ጌታ አምላክ ሆይ! ፍርዶችህ እውነትና ትክክል ናቸው” የሚል ድምፅ ሰማሁ።
8አራተኛው መልአክ ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ፀሐይም ሰዎችን በግለትዋ ለማቃጠል ኀይል ተሰጣት፤ 9ሰዎች በታላቅ ግለት ተቃጠሉ፤ በእነዚህ መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ንስሓ አልገቡም፤ እርሱንም አላከበሩም።
10አምስተኛው መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም መንግሥት ጨለማ ሆነ፤ ሰዎች ከሥቃያቸው የተነሣ ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር፤ 11ከሕመማቸውና ከቊስላቸው የተነሣ የሰማይን አምላክ ተራገሙ፤ ከሥራቸውም ንስሓ አልገቡም።
12ስድስተኛው መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ ለማዘጋጀት የወንዙ ውሃ ደረቀ። 13ከዘንዶው አፍና ከአውሬው አፍ፥ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ። 14እነርሱ ተአምራት የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው፤ እነዚህ መናፍስት ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት ሰዎችን ለመሰብሰብ ወደ ዓለም ነገሥታት ሁሉ ይሄዳሉ።
15“እነሆ! እኔ እንደ ሌባ በድንገት እመጣለሁ! ራቁቱን እንዳይሆንና ኀፍረቱን ሰዎች እንዳያዩበት ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው የተመሰገነ ነው!” #ማቴ. 24፥43-44፤ ሉቃ. 12፥30-40፤ ራዕ. 3፥3።
16መናፍስቱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቡአቸው። #2ነገ. 23፥29፤ ዘካ. 12፥11።
17ሰባተኛው መልአክ ጽዋውን በዐየር ላይ አፈሰሰ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካለው ዙፋን “ተፈጸመ!” የሚል ከፍተኛ ድምፅ ወጣ። 18መብረቅ፥ ድምፅ፥ ነጐድጓድና ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ይህን የመሰለ ታላቅ የምድር መናወጥ ሰው በምድር ላይ ከተፈጠረ ጀምሮ ሆኖ አያውቅም። #ራዕ. 8፥5፤ 11፥13፤19። 19ታላቂቱ ከተማ ከሦስት ተከፈለች፤ የአሕዛብ ከተሞችም ፈራረሱ፤ እግዚአብሔር ታላቂቱን ባቢሎንን አስታወሰ፤ የብርቱ ቊጣው ወይን ጠጅ የተሞላበትን ጽዋ እንድትጠጣም አደረጋት። #ኢሳ. 51፥17። 20ደሴቶች ሁሉ ወዲያ ሸሹ፤ ተራራዎችም አልተገኙም፤ #ራዕ. 6፥14። 21እያንዳንዱ አርባ አምስት ኪሎ ግራም ያኽል የሚመዝን በረዶ ከሰማይ በሰዎች ላይ ወረደ፤ መቅሠፍቱ እጅግ አሠቃቂ ስለ ነበረ ሰዎች በበረዶው መቅሠፍት ምክንያት እግዚአብሔርን ተሳደቡ። #ዘፀ. 9፥23፤ ራዕ. 11፥19።
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 16: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997