የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 119:73-176

መጽሐፈ መዝሙር 119:73-176 አማ05

እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እማር ዘንድ አስተዋይነትን ስጠኝ። በተስፋ ቃልህ ስለምታመን አንተን የሚያከብሩ ሁሉ እኔን በሚያዩበት ጊዜ ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ፍርድህ እውነተኛ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ የቀጣኸኝም እውነተኛ በመሆንህ ነው። ለእኔ ለአገልጋይህ በሰጠኸው የተስፋ ቃል መሠረት ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ያጽናናኝ። በሕግህ ደስ ስለሚለኝ ሕያው ሆኜ ለመኖር እችል ዘንድ ርኅራኄ አድርግልኝ። በሐሰት ያለምክንያት የሚከሱኝ ትዕቢተኞች ይዋረዱ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩ ትእዛዞችህን ያውቁ ዘንድ ወደ እኔ ይምጡ። ኀፍረት እንዳይደርስብኝ ሕግህን በትክክል እንድፈጽም እርዳኝ። የአንተን አዳኝነት በሙሉ ልቤ እመኛለሁ። እምነቴን በቃልህ ላይ አድርጌአለሁ። “መቼ ታጽናናኝ ይሆን?” ብዬ የተስፋ ቃልህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ። ጢስ በሚጤስበት ቤት ተሰቅሎ እንደ ተጨማደደ የወይን ጠጅ አቊማዳ ከጥቅም ውጪ ሆኜአለሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ሕግህን አልረሳሁም። እኔ አገልጋይህ እስከ መቼ ልቈይ? የሚያሳድዱኝንስ የምትቀጣቸው መቼ ነው? ሕግህን የማይጠብቁ ትዕቢተኞች እኔን ለማጥመድ ጒድጓድ ቆፍረዋል። ትእዛዞችህ ሁሉ የጸኑ ናቸው፤ ያለ ምክንያት ስለሚያሳድዱኝ እርዳኝ! እነርሱ ሊገድሉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን ችላ አላልኩም። ሕግህን እጠብቅ ዘንድ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ ሕይወትን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ቃልህ ዘለዓለማዊ ነው፤ በሰማይም ጸንቶ ይኖራል። ቃልህ በዘመናት ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትካት፤ ጸንታም ትኖራለች። ፍጥረቶች ሁሉ አገልጋዮችህ ስለ ሆኑ ትእዛዞችህ እስከ ዛሬ ጸንተው ቈይተዋል። ሕግህ የደስታዬ ምንጭ ባይሆን ኖሮ ከሥቃዬ የተነሣ በሞትኩ ነበር። በሕግህ አማካይነት በሕይወት እንድኖር ጠብቀኸኛልና ሕግህን ከቶ አልረሳም። እኔ የአንተ ስለ ሆንኩ አድነኝ! ትእዛዞችህንም ለማክበር እፈልጋለሁ። ክፉዎች እኔን ለመግደል ያደባሉ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። የሁሉም ነገር ፍጹምነት ወሰን አለው፤ የትእዛዞችህ ፍጹምነት ግን ወሰን የለውም። ሕግህን እጅግ እወዳለሁ፤ ስለ እርሱ ቀኑን ሙሉ አስባለሁ። ትእዛዝህ መቼም ከአእምሮዬ ስለማይጠፋ፥ ከጠላቶቼ ሁሉ ይልቅ እኔን አስተዋይ ያደርገኛል። ሕግህን ዘወትር ስለማሰላስል፥ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥበብ አለኝ። ትእዛዞችህን ሁሉ ስለምፈጽም፥ ከሽማግሌዎች ሁሉ የበለጠ አስተዋይነት አለኝ። ለቃልህ መታዘዝ ስለምፈልግ፥ መጥፎ ጠባይን ሁሉ አስወግጄአለሁ። ያስተማርከኝ አንተ ስለ ሆንክ ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም። ቃልህ እንዴት ጣፋጭ ነው! ከማር ወለላ ይልቅ ይጣፍጣል። ከሕግህ ማስተዋልን አግኝቼአለሁ፤ ስለዚህ የሐሰት መንገድን ሁሉ እጠላለሁ። ቃልህ እንደ መብራት ይመራኛል፤ ለመንገዴም ብርሃን ነው። እውነተኛ ትእዛዞችህን ለመጠበቅ በመሐላ የገባሁትን ቃል አጸናለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ሥቃዬ እጅግ ከባድ ስለ ሆነ በተስፋ ቃልህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ። እግዚአብሔር ሆይ! የምስጋና ጸሎቴን ተቀበል፤ ትእዛዞችህንም አስተምረኝ። ሕይወቴ በአደጋ ላይ ቢሆንም እንኳ ሕግህን አልረሳም ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ ፈቀቅ አላልኩም። ሕግህ ዘለዓለማዊ ሀብቴ ነው፤ የልቤም ደስታ እርሱ ነው። እስከምሞትበት ቀን ድረስ ሕጎችህን ለመፈጸም ወስኜአለሁ፤ በፍጹም ልባቸው በአንተ የማይታመኑትን ወላዋዮች ሁሉ ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድኩ። አንተ ጋሻዬና መሸሸጊያዬ ነህ፤ በቃልህ ተስፋ አደርጋለሁ። እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ፤ እኔ የአምላኬን ትእዛዞች መጠበቅ እፈልጋለሁ። በሕይወት እኖር ዘንድ በተስፋ ቃልህ መሠረት አበርታኝ! ተስፋዬንም አታጨልምብኝ! እድን ዘንድ ደግፈኝ፤ ሁልጊዜም ሕጎችህን እፈጽማለሁ። ዕቅዳቸው ተንኰልና ሐሰት የሞላበት በመሆኑ፥ ከሕግህ የሚያፈነግጡትን ሁሉ ታስወግዳቸዋለህ። ክፉዎችን ሁሉ እንደ ቆሻሻ ነገር ታስወግዳቸዋለህ፤ ስለዚህ ሥርዓትህን እወዳለሁ። አንተን ከመፍራቴ የተነሣ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርድህንም እጅግ ፈራሁት። ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር አድርጌአለሁ፤ ስለዚህ ለሚጨቊኑኝ ጠላቶቼ አትተወኝ! የእኔን የአገልጋይህን ደኅንነት አረጋግጥ፤ እብሪተኞች እንዲያጠቁኝ አታድርግ። አዳኝነትህንና እውነተኛ ቃል ኪዳንህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ። ለእኔ ለአገልጋይህ ፍቅርህን አሳይ፤ ሕጎችህንም አስተምረኝ። እኔ አገልጋይህ ነኝ፤ ሥርዓትህንም እንዳውቅ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ ፍርድህን የምትገልጥበት ጊዜው አሁን ነው። ትእዛዞችህን ከወርቅ ይልቅ አብልጬ እወዳለሁ፤ አዎ፥ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ አብልጬ እወዳለሁ። የአንተ ትእዛዞች ትክክል መሆናቸውን ስለማምን የሐሰትን መንገድ ሁሉ እጠላለሁ። ሥርዓቶችህ አስደናቂዎች ናቸው፤ እኔም በሙሉ ልቤ እታዘዛቸዋለሁ። የቃልህ ትርጒም ብርሃን ይሰጣል፤ ሞኞችን አስተዋዮች ያደርጋል። ትእዛዞችህን በጣም ከመናፈቄ የተነሣ አፌን በጒጒት እከፍታለሁ። ወደ እኔ ተመለስ፤ ለሚወዱህ ሁሉ እንደምታደርገውም ምሕረት አድርግልኝ። በተስፋ ቃልህ መሠረት አካሄዴን አስተካክል፤ ስሕተትም እንዲሠለጥንብኝ አታድርግ። ትእዛዞችህን መጠበቅ እንድችል ከሚጨቊኑኝ ሰዎች እጅ አድነኝ። የፊትህን ብርሃን ለባሪያህ አብራለት፤ ሕግህንም አስተምረኝ። ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ እንባዬ እንደ ወንዝ ውሃ ይፈስሳል። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ እውነተኛ ነህ፤ ፍርድህም ቅን ነው። ሕግህ በፍጹም እውነትና ትክክል ነው። ጠላቶቼ ትእዛዞችህን አለመቀበላቸው በጣም ያበሳጨኛል። የተስፋ ቃልህ እጅግ የታመነ ነው፤ እኔም በጣም እወደዋለሁ። እኔ የማልጠቅምና የተናቅሁ ብሆንም እንኳ ሥርዓትህን አልዘነጋሁም። ጽድቅህ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ ሕግህም ዘለዓለማዊ እውነት ነው። ብዙ ችግርና ጭንቀት ደርሶብኛል፤ ትእዛዞችህ ግን ደስታን ይሰጡኛል። ሥርዓትህ ዘወትር ትክክል ነው፤ በሕይወት ለመኖር እንድችል ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ! በሙሉ ልቤ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ስማኝ፤ እኔም ሕጎችህን እፈጽማለሁ። ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አድነኝም፤ እኔም ሕግህን እጠብቃለሁ። ጎህ ከመቅደዱ በፊት ርዳታህን በመፈለግ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በገባህልኝም ቃል ተስፋ አደርጋለሁ። ቃልህን በማሰላሰል ለማጥናት ሌሊቱን ሙሉ እነቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ስማኝ! በትእዛዝህ መሠረት ሕይወቴን ጠብቅ! ሕግህን የማያከብሩ፥ ክፉ ዕቅድ ዐቅደው የሚያሳድዱኝ ሰዎች ወደ እኔ ቀርበዋል። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን ለእኔ ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህ ሁሉ እውነተኞች ናቸው። ሕጎችህን በማጥናት ለዘለዓለም እንዲጸኑ ያደረግሃቸው መሆናቸውን ከብዙ ጊዜ በፊት ተረድቼአለሁ። እኔ ሕግህን አልረሳሁም፤ ስለዚህ ችግሬን ተመልክተህ አድነኝ። ስለ መብቴ ተከራከርልኝ፤ አድነኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት በሕይወት አኑረኝ። ሕግህን ስለማይፈልጉ ክፉዎች የመዳን ተስፋ የላቸውም። እግዚአብሔር ሆይ! ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ በትእዛዝህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ! የሚጠሉኝና የሚያሳድዱኝ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም። ቃልህን ስለማይጠብቁ፥ ከሐዲዎችን አይቼ ተጸየፍኳቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ትእዛዞችህን እንደምወድ ተመልከት፤ ስለዚህ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ በሕይወት አኑረኝ! ቃልህ በጽኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ትክክለኛ ፍርድህም ዘለዓለማዊ ነው። ባለሥልጣኖች ያለ ምክንያት ያሳድዱኛል፤ እኔ ግን ቃልህን በፍርሃት አከብራለሁ። ብዙ ምርኮ አግኝቶ እንደሚደሰት ሰው በተስፋ ቃልህ እጅግ ደስ ይለኛል። ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁም፤ ሕግህን ግን እወዳለሁ። ስለ እውነተኛ ፍርድህ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን የሚወዱ ፍጹም የሆነ ሰላም አላቸው፤ ከቶ ምንም ነገር ሊያሰናክላቸው አይችልም። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ትእዛዞችህንም እፈጽማለሁ። ትእዛዞችህን እጠብቃለሁ፤ በሙሉ ልቤም እወዳቸዋለሁ። ትእዛዞችህንና ሕግህን አከብራለሁ፤ የምሠራውንም ሁሉ አንተ ታያለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ርዳታህን ለማግኘት ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። ሕግህን ስለምታስተምረኝ ዘወትር አመሰግንሃለሁ። ትእዛዞችህ ሁሉ ትክክለኞች ስለ ሆኑ፥ ስለ ቃልህ እዘምራለሁ። ትእዛዞችህን ስለ መረጥኩ፥ እኔን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ሁን። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን እናፍቃለሁ፤ በሕግህም ደስ ይለኛል። አንተን ለማመስገን እንድችል ዕድሜዬን አርዝምልኝ፤ ሥርዓትህም ረዳቴ ይሁን። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዝብዤአለሁ፤ ነገር ግን ትእዛዞችህን ስላልረሳሁ፥ እኔን አገልጋይህን ፈልገኝ።