እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ። ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ። ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ። ሕግህ ደስታዬ ነውና፣ በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ። እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩህ፣ ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን። ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ። “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ ሥርዐትህን አልረሳሁም። የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው? ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን? በሕግህ መሠረት የማይሄዱ እብሪተኞች ማጥመጃ ጕድጓድ ቈፈሩልኝ። ትእዛዞችህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ ሰዎች ያለ ምክንያት አሳድደውኛልና ርዳኝ። ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤ እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች። ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣ በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ። ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣ በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር። በርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ ሕግህንም ፈልጌአለሁና። ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤ እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ። ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው። አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ። ትእዛዞችህ ምን ጊዜም ስለማይለዩኝ፣ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ። ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ። መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ። አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም። ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው። ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው። የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ። እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በከንፈሬ ያቀረብሁትን የበጎ ፈቃድ ስጦታ ተቀበል፤ ሕግህንም አስተምረኝ። ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም። ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና። ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣ ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ። መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ። የአምላኬን ትእዛዞች እጠብቅ ዘንድ፣ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ራቁ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር። ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ። መሠሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው። የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ ፍርድህንም እፈራለሁ። ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤ እብሪተኞች እንዲጨቍኑኝ አትፍቀድላቸው። ዐይኖቼ ማዳንህን፣ የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። እኔ ባሪያህ ነኝ፤ ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣ ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው። ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ ትእዛዞችህን ወደድሁ። መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤ ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች። የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤ አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል። ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣ አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም። ስምህን ለሚወድዱ ማድረግ ልማድህ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ወደ እኔ ተመልሰህ ምሕረት አድርግልኝ። አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ። ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣ ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ። በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። ሕግህ ባለመከበሩ፤ እንባዬ እንደ ውሃ ይፈስሳል። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ፍርድህም ትክክል ነው። ምስክርነትህን በጽድቅ አዘዝህ፤ እጅግ አስተማማኝም ነው። ጠላቶቼ ቃልህን ዘንግተዋልና፣ ቅናት አሳረረኝ። ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፤ ባሪያህም ወደደው። እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም። ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤ ሕግህም እውነት ነው። መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤ ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው። ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤ በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤ ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ። ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ፤ ምስክርነትህንም እጠብቃለሁ። ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ። ቃልህን አሰላስል ዘንድ፣ ዐይኔ ሌሊቱን ሙሉ ሳይከደን ያድራል። እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ሕግህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። ደባ የሚያውጠነጥኑ ወደ እኔ ቀርበዋል፤ ከሕግህ ግን የራቁ ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህም ሁሉ እውነት ናቸው። ለዘላለም እንደ መሠረትሃቸው፣ ከጥንት ምስክርነትህ ተረድቻለሁ። ሕግህን አልረሳሁምና፣ ሥቃዬን ተመልከት፤ ታደገኝም። ተሟገትልኝ፤ አድነኝም፤ እንደ ቃልህም ሕያው አድርገኝ። ሥርዐትህን ስለማይሹ፣ ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ እንደ ሕግህ ሕያው አድርገኝ። የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ከምስክርህ ዘወር አላልሁም። ቃልህን አይጠብቁምና፣ ከዳተኞችን አይቼ አርቃቸዋለሁ። መመሪያህን እንዴት እንደምወድድ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ። ቃልህ በሙሉ እውነት ነው፤ ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው። ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤ ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ። ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፣ በቃልህ ደስ አለኝ። ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፣ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን የሚወድዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ትእዛዝህንም እፈጽማለሁ። ነፍሴ ምስክርነትህን ትጠብቃለች፤ እጅግ እወድደዋለሁና። መንገዴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነውና፣ ሕግህንና ምስክርነትህን እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ታደገኝ። ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣ ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ። ትእዛዞችህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዞች ናቸውና፣ አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር። ትእዛዝህን መርጫለሁና፣ እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ደስታዬ ነው። አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤ ሕግህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዞችህን አልረሳሁምና፣ ባሪያህን ፈልገው።
መዝሙር 119 ያንብቡ
ያዳምጡ መዝሙር 119
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙር 119:73-176
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos