ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ! እግዚአብሔር የተቤዣቸው ከችግርም ያዳናቸው ሁሉ እንዲሁ ይበሉ። ከባዕድም አገር መልሶ አምጥቶአችኋል፤ ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ሰብስቦአችኋል። አንዳንዶች የመንገዳቸውን አቅጣጫ በመሳት በበረሓ ተንከራተቱ፤ ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ የሚመራቸውን መንገድ ለማግኘት አልቻሉም። ተርበውና ተጠምተው ስለ ነበር፥ ተስፋ ቈረጡ። በመከራቸውም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። እግዚአብሔርም ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ በትክክለኛ መንገድ መራቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ እግዚአብሔርን ያመስግኑ። እርሱ የተጠሙትን ያረካቸዋል፤ የተራቡትንም ብዙ መልካም ነገር በመስጠት ያጠግባቸዋል። ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ውስጥ በሰንሰለትም ታስረው ይኖሩ ነበር። ይህም ሁሉ የደረሰባቸው በልዑል እግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ በማመፃቸውና ምክሩንም በመናቃቸው ነበር። በከባድ ሥራ እንዲጨነቁ አደረጋቸው፤ የሚረዳቸውም ባለማግኘታቸው ተሰናክለው ወደቁ። በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ከነበሩበት ድቅድቅ ጨለማ አወጣቸው፤ የታሰሩበትንም ሰንሰለት ሰባበረ። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ። ከናስ የተሠሩትን በሮች ሰባበረ፤ የብረት መወርወሪያዎችንም ቈራረጠ። የዐመፅን መንገድ በመከተላቸው አንዳዶቹ ሞኞች ነበሩ ሕግን በመተላለፋቸው ምክንያት ተቀጥተውበታል። ምግብ ስላስጠላቸው፥ ለመሞት ተቃርበው ነበር። ከዚህ በኋላ በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። እነርሱን ለመፈወስ ቃሉን ላከ፤ ከሞትም አዳናቸው። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ። የምስጋና መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ በደስታ መዝሙርም ሥራውን ይግለጡ።
መጽሐፈ መዝሙር 107 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 107:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች