ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና። እግዚአብሔር የተቤዣቸው፣ ከጠላት እጅ የታደጋቸው ይህን ይበሉ፤ ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ፣ ከየአገሩ የሰበሰባቸው እንዲህ ይናገሩ። አንዳንዶቹ ጭው ባለ በረሓ ተቅበዘበዙ፤ ወደሚኖሩባት ከተማ የሚያደርስ መንገድ ዐጡ። ተራቡ፤ ተጠሙ፤ ነፍሳቸውም በውስጣቸው ዛለች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ወደሚኖሩባትም ከተማ፣ በቀና መንገድ መራቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቷልና፤ የተራበችውንም ነፍስ በበጎ ነገር አጥግቧል። አንዳንዶቹ በብረት ሰንሰለት ታስረው የተጨነቁ፣ በጨለማ፣ በጥልማሞት ውስጥ የተቀመጡ ነበሩ፤ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በማመፅ፣ የልዑልን ምክር አቃልለዋልና። ስለዚህ በጕልበት ሥራ ልባቸውን አዛለ፤ ተዝለፈለፉ፤ የሚደግፋቸውም አልነበረም። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ከጨለማና ከጥልማሞት አወጣቸው፤ እስራታቸውንም በጠሰላቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ እርሱ የናሱን በሮች ሰብሯልና፤ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጧል። አንዳንዶቹ ከዐመፃቸው የተነሣ ቂሎች ሆኑ፤ ከበደላቸው የተነሣ ችግር ውስጥ ገቡ። ሰውነታቸው የምግብ ዐይነት ሁሉ ተጸየፈች፤ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፤ ከመቃብርም አፋፍ መለሳቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ የምስጋናም መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ ሥራውንም ደስ በሚል ዝማሬ ይግለጹ።
መዝሙር 107 ያንብቡ
ያዳምጡ መዝሙር 107
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙር 107:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች