መዝሙር 107:1-22

መዝሙር 107:1-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና። እግዚአብሔር የተቤዣቸው፣ ከጠላት እጅ የታደጋቸው ይህን ይበሉ፤ ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ፣ ከየአገሩ የሰበሰባቸው እንዲህ ይናገሩ። አንዳንዶቹ ጭው ባለ በረሓ ተቅበዘበዙ፤ ወደሚኖሩባት ከተማ የሚያደርስ መንገድ ዐጡ። ተራቡ፤ ተጠሙ፤ ነፍሳቸውም በውስጣቸው ዛለች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ወደሚኖሩባትም ከተማ፣ በቀና መንገድ መራቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቷልና፤ የተራበችውንም ነፍስ በበጎ ነገር አጥግቧል። አንዳንዶቹ በብረት ሰንሰለት ታስረው የተጨነቁ፣ በጨለማ፣ በጥልማሞት ውስጥ የተቀመጡ ነበሩ፤ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በማመፅ፣ የልዑልን ምክር አቃልለዋልና። ስለዚህ በጕልበት ሥራ ልባቸውን አዛለ፤ ተዝለፈለፉ፤ የሚደግፋቸውም አልነበረም። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ከጨለማና ከጥልማሞት አወጣቸው፤ እስራታቸውንም በጠሰላቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ እርሱ የናሱን በሮች ሰብሯልና፤ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጧል። አንዳንዶቹ ከዐመፃቸው የተነሣ ቂሎች ሆኑ፤ ከበደላቸው የተነሣ ችግር ውስጥ ገቡ። ሰውነታቸው የምግብ ዐይነት ሁሉ ተጸየፈች፤ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፤ ከመቃብርም አፋፍ መለሳቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ የምስጋናም መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ ሥራውንም ደስ በሚል ዝማሬ ይግለጹ።

መዝሙር 107:1-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ! እግዚአብሔር የተቤዣቸው ከችግርም ያዳናቸው ሁሉ እንዲሁ ይበሉ። ከባዕድም አገር መልሶ አምጥቶአችኋል፤ ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ሰብስቦአችኋል። አንዳንዶች የመንገዳቸውን አቅጣጫ በመሳት በበረሓ ተንከራተቱ፤ ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ የሚመራቸውን መንገድ ለማግኘት አልቻሉም። ተርበውና ተጠምተው ስለ ነበር፥ ተስፋ ቈረጡ። በመከራቸውም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። እግዚአብሔርም ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ በትክክለኛ መንገድ መራቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ እግዚአብሔርን ያመስግኑ። እርሱ የተጠሙትን ያረካቸዋል፤ የተራቡትንም ብዙ መልካም ነገር በመስጠት ያጠግባቸዋል። ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ውስጥ በሰንሰለትም ታስረው ይኖሩ ነበር። ይህም ሁሉ የደረሰባቸው በልዑል እግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ በማመፃቸውና ምክሩንም በመናቃቸው ነበር። በከባድ ሥራ እንዲጨነቁ አደረጋቸው፤ የሚረዳቸውም ባለማግኘታቸው ተሰናክለው ወደቁ። በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ከነበሩበት ድቅድቅ ጨለማ አወጣቸው፤ የታሰሩበትንም ሰንሰለት ሰባበረ። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ። ከናስ የተሠሩትን በሮች ሰባበረ፤ የብረት መወርወሪያዎችንም ቈራረጠ። የዐመፅን መንገድ በመከተላቸው አንዳዶቹ ሞኞች ነበሩ ሕግን በመተላለፋቸው ምክንያት ተቀጥተውበታል። ምግብ ስላስጠላቸው፥ ለመሞት ተቃርበው ነበር። ከዚህ በኋላ በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። እነርሱን ለመፈወስ ቃሉን ላከ፤ ከሞትም አዳናቸው። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ። የምስጋና መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ በደስታ መዝሙርም ሥራውን ይግለጡ።

መዝሙር 107:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሃሌ ሉያ! ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ፥ ጌታ የታደጋቸው፥ ከጠላትም እጅ ያዳናቸው ይናገሩ። ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው። በበረሃ፥ በምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፥ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም። ተራቡ፥ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም ዛለች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፥ ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ በቀና መንገድን መራቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የተጠማችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራበችን ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና። በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥ ልባቸው በድካም ተዋረደ፥ ተሰናከሉ የሚረዳቸውም አጡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ ሰንሰለታቸውንም በጣጠሰ። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የናሱን ደጆች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈራርጦአልና። በዓመፅ መንገዳቸው አላዋቂ ሆኑ፥ በጥፋታቸው ተጎሳቆሉ። ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። በተጨነቁ ጊዜም ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከአዘቅትም አዳናቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ።

መዝሙር 107:1-22

መዝሙር 107:1-22 NASVመዝሙር 107:1-22 NASV