የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 107

107
ክፍል አምስት
(መዝ. 107—150)
ስለ እግዚአብሔር ቸርነት የሚቀርብ ምስጋና
1ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ
እግዚአብሔርን አመስግኑ! #1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 5፥13፤ 7፥3፤ ዕዝ. 3፥11፤ መዝ. 100፥5፤ 106፥1፤ 118፥1፤ 136፥1፤ ኤር. 33፥11።
2እግዚአብሔር የተቤዣቸው ከችግርም ያዳናቸው ሁሉ እንዲሁ ይበሉ።
3ከባዕድም አገር መልሶ አምጥቶአችኋል፤
ከምሥራቅና ከምዕራብ፥
ከሰሜንና ከደቡብ ሰብስቦአችኋል።
# 107፥3 ከደቡብ ወይም ከሜዲቴራኒያን ባሕር።
4አንዳንዶች የመንገዳቸውን አቅጣጫ በመሳት
በበረሓ ተንከራተቱ፤
ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ የሚመራቸውን መንገድ
ለማግኘት አልቻሉም።
5ተርበውና ተጠምተው ስለ ነበር፥
ተስፋ ቈረጡ።
6በመከራቸውም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤
እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው።
7እግዚአብሔርም ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ
በትክክለኛ መንገድ መራቸው።
8ለሰው ልጆች ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ
እግዚአብሔርን ያመስግኑ።
9እርሱ የተጠሙትን ያረካቸዋል፤
የተራቡትንም ብዙ መልካም ነገር በመስጠት ያጠግባቸዋል።
10ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ ጥቅጥቅ ባለ
ጨለማ ውስጥ
በሰንሰለትም ታስረው ይኖሩ ነበር።
11ይህም ሁሉ የደረሰባቸው በልዑል እግዚአብሔር
ትእዛዝ ላይ በማመፃቸውና
ምክሩንም በመናቃቸው ነበር።
12በከባድ ሥራ እንዲጨነቁ አደረጋቸው፤
የሚረዳቸውም ባለማግኘታቸው ተሰናክለው ወደቁ።
13በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤
እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው።
14ከነበሩበት ድቅድቅ ጨለማ አወጣቸው፤
የታሰሩበትንም ሰንሰለት ሰባበረ።
15ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና
ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ።
16ከናስ የተሠሩትን በሮች ሰባበረ፤
የብረት መወርወሪያዎችንም ቈራረጠ።
17የዐመፅን መንገድ በመከተላቸው አንዳዶቹ ሞኞች ነበሩ
ሕግን በመተላለፋቸው ምክንያት ተቀጥተውበታል።
18ምግብ ስላስጠላቸው፥
ለመሞት ተቃርበው ነበር።
19ከዚህ በኋላ በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤
እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው።
20እነርሱን ለመፈወስ ቃሉን ላከ፤
ከሞትም አዳናቸው።
21ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና
ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ።
22የምስጋና መሥዋዕት ያቅርቡለት፤
በደስታ መዝሙርም ሥራውን ይግለጡ።
23አንዳንዶች በመርከብ ተሳፍረው በታላቅ በባሕር ላይ እየተጓዙ
ንግዳቸውን ያካሂዱ ነበር።
24እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ አዩ፤
በጥልቅ ባሕርም ውስጥ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ተመለከቱ።
25ትእዛዝ በሰጠ ጊዜ ዐውሎ ነፋስ ነፈሰ፤
ማዕበሉም ተንቀሳቀሰ።
26መርከበኞቹ በሞገዱ ኀይል ተገፍትረው ወደ ላይ ወጡ፤
ተመልሰውም ወደ ጥልቁ ወረዱ፤
ወደ ፊትና ወደ ኋላ ተዋከቡ።
27እንደ ሰካራም ዞረባቸው፤ ተንገዳገዱም፤
የማስተዋል ችሎታቸው ሁሉ ጠፋ።
28በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤
እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው።
29ዐውሎ ነፋሱንና
ማዕበሉን ጸጥ አደረገ።
30በጸጥታውም ምክንያት ደስ አላቸው፤
ወደ ፈለጉትም ወደብ በሰላም አደረሳቸው።
31ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና
ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ።
32በሕዝብ ጉባኤ መካከል ታላቅነቱንም ያብሥሩ፤
በሽማግሌዎች ሸንጎ ያመስግኑት።
33እግዚአብሔር ወንዞች ፈጽመው እንዲደርቁ፥
ምንጮችም እንዳይፈስሱ አደረገ።
34እዚያ ከሚኖሩት ሰዎች ክፋት የተነሣ
ፍሬያማዋን አገር እንደ ጨው ምድር የማታፈራ አደረጋት።
35እንደገናም በበረሓው ብዙ ኲሬዎች እንዲኖሩ፥
በደረቁም ምድር ብዙ ምንጮች እንዲገኙ አደረገ።
36የተራቡ ሕዝቦች በዚያ እንዲሰፍሩ አደረገ፤
እነርሱም የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሠሩ።
37በእርሻዎች ላይ እህልን ዘሩ፤ ወይንን ተከሉ፤
ብዙ መከርም ሰበሰቡ።
38ሕዝቡን ባረካቸው፤ ብዙ ልጆችም ወለዱ፤
የከብቶቻቸውም ቊጥር እንዳያንስ አደረገ።
39በጭቈና፥ በችግርና በሐዘን ተሸንፈው
በተዋረዱ ጊዜ ግን፥
40እግዚአብሔር ልዑላኑን አዋረደ፤
በምድረ በዳም አሸዋ ውስጥ እንዲንከራተቱ አደረገ።
41ችግረኞችንም ከሥቃያቸው አወጣቸው፤
እንደ በግ መንጋ የበዙ ልጆችንም ሰጣቸው።
42ቅኖች ይህን በማየት ደስ ይላቸዋል፤
ክፉዎች ግን ዐፍረው ዝም ይላሉ።
43ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ ይህን ያስተውሉ፤
ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን የፍቅር ሥራ ይገንዘቡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ