ዋልያዎች በከፍተኛ ተራራዎች ላይ ይገኛሉ፤ ሽኮኮዎችም በተሰነጠቁ አለቶች ውስጥ ይኖራሉ። ጨረቃን የወቅቶች ምልክት እንድትሆን፥ ፀሐይ የሚጠልቅበትን ጊዜ እንዲያውቅ አድርገሃል። አንተ ጨለማን ፈጠርክ፤ ሌሊትም ሆነ፤ በጨለማም የዱር አውሬዎች ሁሉ ይወጣሉ። እግዚአብሔር የሚያዘጋጀውን ምግብ ሲያድኑ የአንበሳ ደቦሎች ያገሣሉ። ፀሐይ በሚወጣበት ጊዜ ሾልከው ይሄዳሉ፤ ተመልሰው በየመኖሪያቸው ውስጥ ይተኛሉ። ከዚህ በኋላ ሰዎች ለሥራ ይሰማራሉ፤ እስከሚመሽም ድረስ ሲሠሩ ይውላሉ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ብዙ ነገሮችን ፈጥረሃል፤ ሁሉንም በጥበብ አድርገሃል፤ ምድር አንተ በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች። ከቊጥር በላይ በሆኑ ታላላቅና ታናናሽ ሕያዋን ፍጥረቶች የተሞላው ትልቁና ሰፊው ባሕር እነሆ፥ በላዩ መርከቦች ይመላለሳሉ፤ በውስጡም አንተ የፈጠርከው ሌዋታን የተባለ ታላቅ ዘንዶ ይጫወታል። እነዚህ ሁሉ ምግባቸውን በየጊዜው እንድትሰጣቸው ተስፋ የሚያደርጉት አንተን ነው። አንተ ምግብ ስትሰጣቸው እነርሱም ይመገባሉ፤ አንተ እጅህን ስትዘረጋ እነርሱም መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ በልተው ይጠግባሉ። አንተ ስትለያቸው ሁሉም ይደነግጣሉ፤ እስትንፋሳቸውን ስትወስድባቸውም ይሞታሉ፤ ወደ ተገኙበትም ዐፈር ይመለሳሉ። እስትንፋስ ስትሰጣቸው ግን ይፈጠራሉ፤ ለምድርም አዲስ ሕይወት ትሰጣለህ። የእግዚአብሔር ክብር ለዘለዓለም ይኑር! እግዚአብሔር በፈጠረው ነገር ሁሉ ደስ ይበለው። ምድርን ሲመለከት ትንቀጠቀጣለች፤ ተራራዎችን ሲነካ እነርሱም ይጤሳሉ። በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ድረስ ለአምላኬ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ። ደስታዬ በእርሱ ስለ ሆነ እርሱም በማቀርብለት የተመስጦ ጸሎት ደስ ይበለው። ኃጢአተኞች ከምድር ላይ ይጥፉ! ግፍ አድራጊዎችም ይደምሰሱ!
መጽሐፈ መዝሙር 104 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 104:18-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች