መዝሙር 104:18-35

መዝሙር 104:18-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እግ​ሮ​ቹም በእ​ግር ብረት ሰለ​ሰሉ፥ ሰው​ነ​ቱም ከብ​ረት አመ​ለ​ጠች። ቃሉ ሳይ​ደ​ርስ፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ፈተ​ነው። ንጉሥ ላከ፥ ፈታ​ውም፥ የሕ​ዝ​ብም አለቃ አድ​ርጎ ሾመው። የቤቱ ጌታም አደ​ረ​ገው፥ በገ​ን​ዘቡ ሁሉ ላይ ገዢ አደ​ረ​ገው፥ አለ​ቆ​ቹን ሁሉ እንደ እርሱ ይገ​ሥጽ ዘንድ፥ ሽማ​ግ​ሌ​ዎ​ቹ​ንም እንደ እርሱ ጥበ​በ​ኞች ያደ​ር​ጋ​ቸው ዘንድ። እስ​ራ​ኤ​ልም ወደ ግብፅ ገባ፥ ያዕ​ቆ​ብም በካም ምድር ተቀ​መጠ። ሕዝ​ቡ​ንም እጅግ አበ​ዛ​ቸው፥ ከጠ​ላ​ቶ​ቻ​ቸ​ውም ይልቅ አበ​ረ​ታ​ቸው። ሕዝ​ቡን ይጠሉ ዘንድ በባ​ሪ​ያ​ዎ​ቹም ላይ ይተ​ነ​ኰሉ ዘንድ ልባ​ቸ​ውን ለወጠ። ባሪ​ያ​ውን ሙሴን፥ የመ​ረ​ጠ​ው​ንም አሮ​ንን ላከ። የተ​አ​ም​ራ​ቱን ቃል በላ​ያ​ቸው ድን​ቁ​ንም በካም ምድር አደ​ረገ። ጨለ​ማ​ንም ላከ ጨለ​መ​ባ​ቸ​ውም፤ ቃሉ​ንም መራራ አደ​ረ​ጉት። ውኃ​ቸ​ውን ደም አደ​ረገ፥ ዓሦ​ቻ​ቸ​ው​ንም ገደለ። ምድ​ራ​ቸው በን​ጉ​ሦ​ቻ​ቸው ቤቶች ጓጕ​ን​ቸ​ሮ​ችን አወ​ጣች። እርሱ ተና​ገረ፥ የውሻ ዝንብ ትን​ኝም በም​ድ​ራ​ቸው ሁሉ መጡ። ዝና​ባ​ቸ​ውን በረዶ አደ​ረ​ገው፥ እሳ​ትም በም​ድ​ራ​ቸው ነደደ። ወይ​ና​ቸ​ው​ንና በለ​ሳ​ቸ​ውን መታ፥ የሀ​ገ​ራ​ቸ​ው​ንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። ተና​ገረ፥ አን​በ​ጣም፥ ስፍር ቍጥር የሌ​ለ​ውም ኵብ​ኵባ መጣ፥ የም​ድ​ራ​ቸ​ው​ንም ፍሬ ሁሉ በላ የተ​ግ​ባ​ራ​ቸ​ውን ሁሉ መጀ​መ​ሪያ በላ፥

መዝሙር 104:18-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ረዣዥሙ ተራራ የዋሊያ መኖሪያ፣ የዐለቱም ዋሻዎች የሽኮኮ መሸሸጊያ ናቸው። ጨረቃን የወቅቶች መለያ አደረግሃት፤ ፀሓይም የምትጠልቅበትን ጊዜ ታውቃለች። ጨለማን ታመጣለህ፤ ሌሊትም ይሆናል፤ የዱር አራዊትም ሁሉ በዚህ ጊዜ ወጥተው ይራወጣሉ። የአንበሳ ግልገሎች ምግብ ፍለጋ ይጮኻሉ፤ የሚበሉትንም ከእግዚአብሔር ይሻሉ። ፀሓይ በወጣች ጊዜም ይመለሳሉ፤ በየጐሬያቸውም ገብተው ይተኛሉ። ሰውም ወደ ሥራው ይሄዳል፤ እስኪመሽም በተግባሩ ላይ ይሰማራል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ሰፊና የተንጣለለች ናት፤ ታላላቅና ታናናሽ እንስሳት፣ ስፍር ቍጥር የሌላቸውም የሚርመሰመሱ ፍጥረታት በውስጧ አሉ። መርከቦች በላይዋ ይመላለሳሉ፤ አንተ የፈጠርኸውም ሌዋታን በውስጧ ይፈነጫል። ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸው ዘንድ፣ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በሰጠሃቸውም ጊዜ፣ አንድ ላይ ያከማቻሉ፤ እጅህንም ስትዘረጋ፣ በመልካም ነገር ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር፣ በድንጋጤ ይሞላሉ፤ እስትንፋሳቸውንም ስትወስድባቸው ይሞታሉ፤ ወደ ዐፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ስትልክ፣ እነርሱ ይፈጠራሉ፤ የምድርንም ገጽ ታድሳለህ። የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይበለው፤ እርሱ ምድርን ሲመለከት፣ ትንቀጠቀጣለች፤ ተራሮችም እርሱ ሲዳስሳቸው ይጤሳሉ። በሕይወት ሳለሁ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ቆሜ እስከ ሄድሁ ድረስም አምላኬን እወድሳለሁ። እኔ በእግዚአብሔር ደስ እንደሚለኝ፣ የልቤ ሐሳብ እርሱን ደስ ያሠኘው። ኃጥኣን ከምድር ገጽ ይጥፉ፤ ዐመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ።

መዝሙር 104:18-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዋልያዎች በከፍተኛ ተራራዎች ላይ ይገኛሉ፤ ሽኮኮዎችም በተሰነጠቁ አለቶች ውስጥ ይኖራሉ። ጨረቃን የወቅቶች ምልክት እንድትሆን፥ ፀሐይ የሚጠልቅበትን ጊዜ እንዲያውቅ አድርገሃል። አንተ ጨለማን ፈጠርክ፤ ሌሊትም ሆነ፤ በጨለማም የዱር አውሬዎች ሁሉ ይወጣሉ። እግዚአብሔር የሚያዘጋጀውን ምግብ ሲያድኑ የአንበሳ ደቦሎች ያገሣሉ። ፀሐይ በሚወጣበት ጊዜ ሾልከው ይሄዳሉ፤ ተመልሰው በየመኖሪያቸው ውስጥ ይተኛሉ። ከዚህ በኋላ ሰዎች ለሥራ ይሰማራሉ፤ እስከሚመሽም ድረስ ሲሠሩ ይውላሉ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ብዙ ነገሮችን ፈጥረሃል፤ ሁሉንም በጥበብ አድርገሃል፤ ምድር አንተ በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች። ከቊጥር በላይ በሆኑ ታላላቅና ታናናሽ ሕያዋን ፍጥረቶች የተሞላው ትልቁና ሰፊው ባሕር እነሆ፥ በላዩ መርከቦች ይመላለሳሉ፤ በውስጡም አንተ የፈጠርከው ሌዋታን የተባለ ታላቅ ዘንዶ ይጫወታል። እነዚህ ሁሉ ምግባቸውን በየጊዜው እንድትሰጣቸው ተስፋ የሚያደርጉት አንተን ነው። አንተ ምግብ ስትሰጣቸው እነርሱም ይመገባሉ፤ አንተ እጅህን ስትዘረጋ እነርሱም መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ በልተው ይጠግባሉ። አንተ ስትለያቸው ሁሉም ይደነግጣሉ፤ እስትንፋሳቸውን ስትወስድባቸውም ይሞታሉ፤ ወደ ተገኙበትም ዐፈር ይመለሳሉ። እስትንፋስ ስትሰጣቸው ግን ይፈጠራሉ፤ ለምድርም አዲስ ሕይወት ትሰጣለህ። የእግዚአብሔር ክብር ለዘለዓለም ይኑር! እግዚአብሔር በፈጠረው ነገር ሁሉ ደስ ይበለው። ምድርን ሲመለከት ትንቀጠቀጣለች፤ ተራራዎችን ሲነካ እነርሱም ይጤሳሉ። በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ድረስ ለአምላኬ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ። ደስታዬ በእርሱ ስለ ሆነ እርሱም በማቀርብለት የተመስጦ ጸሎት ደስ ይበለው። ኃጢአተኞች ከምድር ላይ ይጥፉ! ግፍ አድራጊዎችም ይደምሰሱ!

መዝሙር 104:18-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ረጃጅም ተራራዎች ለዋላዎች፥ ድንጋዮችም ለእሽኮኮች መሸሻ ናቸው። ወቅቶችን ለማመልከት ጨረቃን አደረግህ፥ ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል። ጨለማን ታስቀምጣለህ፥ ሌሊትም ይሆናል፥ በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል። የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ፥ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ። ፀሐይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ፥ በየዋሻቸውም ይተኛሉ። ሰው ወደ ተግባሩ፥ እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል። አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፥ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፥ በዚያ ስፍር ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ። በዚያ ላይ መርከቦች ይሄዳሉ፥ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ያጫውትሃል። ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በምትሰጣቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፥ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፥ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ። የጌታ ክብር ለዘለዓለም ይሁን፥ ጌታ በሥራው ደስ ይለዋል። ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፥ ተራሮችን ይዳስሳል፥ ይጤሳሉም። በሕይወቴ ሳለሁ ለጌታ እቀኛለሁ፥ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ። ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥ እኔም በጌታ ደስ ይለኛል። ኀጥኣን ከምድር ይጥፉ፥ ዓመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ። ሃሌ ሉያ።