ጠባየ መልካምን ሚስት ማን ሊያገኛት ይችላል? እርስዋ ከዕንቊ ይልቅ የከበረች ናት። ባልዋ ይተማመንባታል፤ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አያጣም። በምትኖርበት ዘመን ሁሉ መልካም ነገር ታደርግለታለች እንጂ ክፉ ነገር አታደርግበትም። ከሱፍ ክርና ከበፍታ ልብስ በመስፋት ደስ እያላት በሥራ ትጠመዳለች። እንደ ነጋዴ መርከብ ወደ ሩቅ ስፍራዎች በመሄድ ልዩ ልዩ ዐይነት ምግቦችን ትሰበስባለች። ለቤተሰብዋ ምግብ ለማዘጋጀትና ለሠራተኞችዋ ሥራ ለማከፋፈል ገና ሳይነጋ ትነሣለች። ደኅና መሬት ፈልጋ ትገዛለች፤ ሠርታ በምታገኘውም ገንዘብ የወይን አትክልት ቦታ ታዘጋጃለች። እርስዋ ትጉህ ሠራተኛ ከመሆንዋም በላይ በሥራዋ ብርቱ ናት። የምትሠራው ሁሉ ዋጋ እንዳለው ታውቃለች፤ ማታም ስትሠራ ስለምታመሽ መብራትዋ አይጠፋም፤ የነደፈችውን አመልማሎ በራስዋ እንዝርት ፈትላ ልብስዋን ትሠራለች። ለድኾችና ለችግረኞች ትለግሣለች። ቤተሰብዋ በሙሉ ሞቃት ልብስ ስላለው በረዶ እንኳ ቢዘንብ አትሠጋም። የአልጋ ልብስ ትሠራለች፤ ከቀይ ሐር የተሠራ ምርጥ ልብስም ትለብሳለች። ባልዋ የአገር ሽማግሌዎች በሚሰበሰቡበት ሸንጎ የተከበረ ነው። የበፍታ ልብስ እየሠራች ትሸጣለች፤ ለነጋዴዎችም ድግ ታስረክባለች። እርስዋ ብርቱና የተከበረች ናት፤ በመጪው ጊዜ ሁሉ ደስ ብሎአት ትኖራለች። በጥበብ ትናገራለች፤ በቅን መንፈስ ትመክራለች። ዘወትር በሥራ ተጠምዳ ቤተሰብዋን ስለምትንከባከብ ስንፍና አይገኝባትም። ልጆችዋ አድናቆታቸውን ይገልጡላታል፤ ባልዋም ያመሰግናታል፤ “ጥሩ ሚስቶች የሆኑ ብዙ ሴቶች አሉ፤ አንቺ ግን ከሁሉም ትበልጫለሽ” ይላታል። ቊንጅና ከንቱ ነው፤ ውበትም ይጠፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን ልትመሰገን ይገባታል። እርስዋ ለምታደርገው ነገር ሁሉ አመስግኑአት፤ ስለ መልካም ሥራዋ በሰዎች ሁሉ ዘንድ ልትከበር ይገባታል።
መጽሐፈ ምሳሌ 31 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ምሳሌ 31:10-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos