የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 31

31
ለንጉሥ የተሰጠ ምክር
1ከዚህ የሚከተለው ለማሳው ንጉሥ ለልሙኤል እናቱ የሰጠችው ምክር ነው።
2“በስእለት የወለድኩህ ልጄ ልሙኤል ሆይ! ስማኝ፦ አድምጠኝ፤ 3ጒልበትህን በዝሙት አትጨርስ፤ ይህ ድርጊት ነገሥታትን ሳይቀር አዋርዷል።
4“ልሙኤል ሆይ! ነገሥታት ወይን ጠጅ ይጠጡ ዘንድ፥ መሳፍንትም ጠንካራ መጠጥን ለመጠጣት ይጓጉ ዘንድ ተገቢ አይደለም። 5እነርሱ ጠጥተው ሲሰክሩ ሕግን ይረሳሉ፤ የተቸገሩትንም ሰዎች መብት ችላ ይላሉ።
6“በሞት ጣር ላይ ለሚገኙና በሥቃይ ኑሮ ወይንና የሚያሰክር መጠጥ ስጡአቸው። 7እነርሱ ድኽነታቸውንና ሥቃያቸውን እንዲረሱ ይጠጡ።
8“ልጄ ሆይ! ስለ ራሳቸው ችግር መናገር ለማይችሉ ሰዎች አንተ ተናገርላቸው፤ ፍርድ አጥተው ለተጨነቁ ሰዎች መብታቸውን አስከብርላቸው፤ 9ስለ እነርሱ ተናገር፤ ትክክለኛ ፍርድም ፍረድላቸው፤ የድኾችንና የችግረኞችን መብት ጠብቅ።”
ባለሙያ ሚስት
10ጠባየ መልካምን ሚስት ማን ሊያገኛት ይችላል? እርስዋ ከዕንቊ ይልቅ የከበረች ናት።
11ባልዋ ይተማመንባታል፤ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አያጣም።
12በምትኖርበት ዘመን ሁሉ መልካም ነገር ታደርግለታለች እንጂ ክፉ ነገር አታደርግበትም።
13ከሱፍ ክርና ከበፍታ ልብስ በመስፋት ደስ እያላት በሥራ ትጠመዳለች። 14እንደ ነጋዴ መርከብ ወደ ሩቅ ስፍራዎች በመሄድ ልዩ ልዩ ዐይነት ምግቦችን ትሰበስባለች። 15ለቤተሰብዋ ምግብ ለማዘጋጀትና ለሠራተኞችዋ ሥራ ለማከፋፈል ገና ሳይነጋ ትነሣለች።
16ደኅና መሬት ፈልጋ ትገዛለች፤ ሠርታ በምታገኘውም ገንዘብ የወይን አትክልት ቦታ ታዘጋጃለች።
17እርስዋ ትጉህ ሠራተኛ ከመሆንዋም በላይ በሥራዋ ብርቱ ናት።
18የምትሠራው ሁሉ ዋጋ እንዳለው ታውቃለች፤ ማታም ስትሠራ ስለምታመሽ መብራትዋ አይጠፋም፤
19የነደፈችውን አመልማሎ በራስዋ እንዝርት ፈትላ ልብስዋን ትሠራለች።
20ለድኾችና ለችግረኞች ትለግሣለች።
21ቤተሰብዋ በሙሉ ሞቃት ልብስ ስላለው በረዶ እንኳ ቢዘንብ አትሠጋም።
22የአልጋ ልብስ ትሠራለች፤ ከቀይ ሐር የተሠራ ምርጥ ልብስም ትለብሳለች።
23ባልዋ የአገር ሽማግሌዎች በሚሰበሰቡበት ሸንጎ የተከበረ ነው።
24የበፍታ ልብስ እየሠራች ትሸጣለች፤ ለነጋዴዎችም ድግ ታስረክባለች።
25እርስዋ ብርቱና የተከበረች ናት፤ በመጪው ጊዜ ሁሉ ደስ ብሎአት ትኖራለች።
26በጥበብ ትናገራለች፤ በቅን መንፈስ ትመክራለች።
27ዘወትር በሥራ ተጠምዳ ቤተሰብዋን ስለምትንከባከብ ስንፍና አይገኝባትም።
28ልጆችዋ አድናቆታቸውን ይገልጡላታል፤ ባልዋም ያመሰግናታል፤
29“ጥሩ ሚስቶች የሆኑ ብዙ ሴቶች አሉ፤ አንቺ ግን ከሁሉም ትበልጫለሽ” ይላታል።
30ቊንጅና ከንቱ ነው፤ ውበትም ይጠፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን ልትመሰገን ይገባታል።
31እርስዋ ለምታደርገው ነገር ሁሉ አመስግኑአት፤ ስለ መልካም ሥራዋ በሰዎች ሁሉ ዘንድ ልትከበር ይገባታል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ