የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ምሳሌ 31:10-31

ምሳሌ 31:10-31 NASV

ጠባየ መልካምን ሚስት ማን ያገኛታል? ከቀይ ዕንቍ እጅግ ትበልጣለች። ባሏ ሙሉ በሙሉ ይተማመንባታል፤ የሚጐድልበትም ነገር የለም። በሕይወት ዘመኗ ሁሉ፣ መልካም ታደርግለታለች እንጂ አትጐዳውም። የበግ ጠጕርና የተልባ እግር መርጣ፣ ሥራ በሚወድዱ እጆቿ ትፈትላቸዋለች። እንደ ንግድ መርከብ፣ ምግቧን ከሩቅ ትሰበስባለች። ገና ሳይነጋ ትነሣለች፤ ለቤተ ሰቧ ምግብ፣ ለሴት አገልጋዮቿም ድርሻቸውን ትሰጣለች። ራሷ አስባ የዕርሻ መሬት ትገዛለች፤ በምታገኘውም ገንዘብ ወይን ትተክላለች። ብርታትን ታጥቃ ሥራዋን ታከናውናለች፤ ክንዶቿም ለሥራ ብርቱ ናቸው። ሥራዋ ትርፋማ መሆኑን ታስተውላለች፤ በሌሊትም መብራቷ አይጠፋም። በእጇ እንዝርት ትይዛለች፤ በጣቶቿም ዘንጉን ታሾራለች። ክንዶቿን ለድኾች ትዘረጋለች፣ እጆቿንም ለችግረኞች ፈታ ታደርጋለች። በረዶ ቢጥል ለቤተ ሰዎቿ አትሠጋም፤ ሁሉም ቀይ ልብስ ለብሰዋልና። ለመኝታዋ የዐልጋ ልብስ ትሠራለች፤ ቀጭን በፍታና ሐምራዊ ልብስ ለብሳለች። ባሏ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በአደባባይ በተቀመጠ ጊዜ የተከበረ ነው። የበፍታ መጐናጸፊያዎችን ሠርታ ትሸጣለች፤ ለነጋዴዎችም ድግ ታቀርባለች። ብርታትንና ሞገስን ተጐናጽፋለች፤ መጪውን ጊዜ በደስታ ትቀበላለች። በጥበብ ትናገራለች፤ በአንደበቷም ቀና ምክር አለ። የቤተ ሰቦቿን ጕዳይ በትጋት ትከታተላለች፤ የስንፍና እንጀራ አትበላም። ልጆቿ ተነሥተው ቡርክት ይሏታል፤ ባሏም እንዲሁ፣ ሲያመሰግናትም እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ሴቶች መልካም አድርገዋል፤ አንቺ ግን ሁሉንም ትበልጫለሽ።” ቍንጅና አታላይ ነው፤ ውበትም ይረግፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን የተመሰገነች ናት። የሚገባትን ሽልማት ስጧት፤ ሥራዋም በየአደባባዩ ያስመስግናት።