ኦሪት ዘኊልቊ 7:1-10

ኦሪት ዘኊልቊ 7:1-10 አማ05

ሙሴ የመገናኛውን ድንኳን ተክሎ በፈጸመበት ቀን ድንኳኑንና የመገልገያ ዕቃዎቹን፥ መሠዊያውንና የመገልገያ ዕቃዎቹን፥ ዘይት በመቀባት ቀደሳቸው፤ ከዚያ በኋላ በእስራኤል ነገዶች መካከል የጐሣ አለቆች የሆኑት ማለትም በሕዝብ ቈጠራ ጊዜ ኀላፊነት የነበራቸው ሁሉ፥ መባቸውን ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ ያቀረቡአቸውም መባዎች በየሁለቱ አለቆች ስም አንድ ሠረገላ፥ እንዲሁም በእያንዳንዱ አለቃ ስም አንድ በሬ ሆኖ፥ ስድስት ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት በሬዎች ነበሩ፤ እነዚህንም መባዎች በመገናኛው ድንኳን ፊት አቀረቡ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚከናወነው ተግባር መገልገያ ይሆኑ ዘንድ እነዚህን መባዎች ተቀበል፤ ለእያንዳንዳቸው አገልግሎት በሚያስፈልጋቸው መጠን መድበህ ለሌዋውያን ስጣቸው።” ስለዚህ ሙሴ ሠረገሎቹንና በሬዎቹን ተቀብሎ ለሌዋውያን ሰጣቸው። ለጌርሾናውያን አገልግሎት አስፈላጊ የሆነውን ሁለት ሠረገሎችንና አራት በሬዎችን ሰጠ። ለሜራሪያውያን አራት ሠረገሎችንና ስምንት በሬዎችን ሰጠ። የእነርሱም አገልግሎት የሚከናወነው የአሮን ልጅ በሆነው በኢታማር ኀላፊነት ነበር። በእነርሱ ኀላፊነት የሚጠበቁት ንዋያተ ቅድሳት በትከሻቸው የሚሸከሙአቸው ስለ ሆኑ ሙሴ ለቀዓታውያን ሠረገሎችንም ሆነ በሬዎችን አልሰጣቸውም። መሠዊያው በተባረከበት ቀን መሪዎቹ መሠዊያውን ለመቀደስ በመሠዊያው ፊት ቊርባን አቀረቡ።