ዘኍልቍ 7:1-10

ዘኍልቍ 7:1-10 NASV

ሙሴ የማደሪያ ድንኳኑን ተክሎ ካበቃ በኋላ ማደሪያ ድንኳኑንና ዕቃዎቹን ሁሉ ቀባቸው፤ ቀደሳቸውም፤ እንደዚሁም መሠዊያውንና ዕቃዎቹን በሙሉ ቀባቸው፤ ቀደሳቸውም። ከዚያም የእስራኤል አለቆች ሆነው ከተቈጠሩት ነገዶች ኀላፊዎች የነበሩት የየቤተ ሰቡ መሪዎች ስጦታቸውን አቀረቡ። ስድስት የተሸፈኑ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት በሬዎች ይኸውም ከእያንዳንዱ አለቃ አንዳንድ በሬ እንዲሁም ከየሁለቱ አለቆች አንድ ሠረገላ ስጦታ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ፊት አመጡ፤ እነዚህንም በማደሪያው ድንኳን ፊት አቀረቧቸው። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በመገናኛውም ድንኳን ለአገልግሎት እንዲውሉ እነዚህን ከእነርሱ ተቀበል፤ ለእያንዳንዳቸውም ለአገልግሎታቸው በሚያስፈልጋቸው መጠን ለሌዋውያኑ ስጣቸው።” ስለዚህ ሙሴ ሠረገሎቹንና በሬዎቹን ወስዶ ለሌዋውያኑ ሰጣቸው፤ ለጌርሶናውያን ለአገልግሎታቸው በሚያስፈልጋቸው መጠን ሁለት ሠረገሎችና አራት በሬዎች ሰጠ። ለሜራሪያውያንም ለአገልግሎታቸው በሚያስፈልጋቸው መጠን አራት ሠረገሎችና ስምንት በሬዎች ሰጠ። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ኀላፊነት የሚመሩ ነበሩ። በኀላፊነት የተሰጧቸውን ንዋያተ ቅድሳት በትከሻቸው መሸከም ስለ ነበረባቸው፣ ሙሴ ለቀዓታውያን ምንም አልሰጣቸውም። መሠዊያው በተቀባበት ቀን አለቆች የመሠዊያውን መቀደስ ምክንያት በማድረግ ስጦታዎችን አመጡ፤ በመሠዊያውም ፊት አቀረቡ።