የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 7

7
የሕዝቡ አለቆች ያቀረቡት ስጦታ
1ሙሴ የመገናኛውን ድንኳን ተክሎ በፈጸመበት ቀን ድንኳኑንና የመገልገያ ዕቃዎቹን፥ መሠዊያውንና የመገልገያ ዕቃዎቹን፥ ዘይት በመቀባት ቀደሳቸው፤ 2ከዚያ በኋላ በእስራኤል ነገዶች መካከል የጐሣ አለቆች የሆኑት ማለትም በሕዝብ ቈጠራ ጊዜ ኀላፊነት የነበራቸው ሁሉ፥ 3መባቸውን ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ ያቀረቡአቸውም መባዎች በየሁለቱ አለቆች ስም አንድ ሠረገላ፥ እንዲሁም በእያንዳንዱ አለቃ ስም አንድ በሬ ሆኖ፥ ስድስት ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት በሬዎች ነበሩ፤ እነዚህንም መባዎች በመገናኛው ድንኳን ፊት አቀረቡ። 4እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 5“በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚከናወነው ተግባር መገልገያ ይሆኑ ዘንድ እነዚህን መባዎች ተቀበል፤ ለእያንዳንዳቸው አገልግሎት በሚያስፈልጋቸው መጠን መድበህ ለሌዋውያን ስጣቸው።” 6ስለዚህ ሙሴ ሠረገሎቹንና በሬዎቹን ተቀብሎ ለሌዋውያን ሰጣቸው። 7ለጌርሾናውያን አገልግሎት አስፈላጊ የሆነውን ሁለት ሠረገሎችንና አራት በሬዎችን ሰጠ። 8ለሜራሪያውያን አራት ሠረገሎችንና ስምንት በሬዎችን ሰጠ። የእነርሱም አገልግሎት የሚከናወነው የአሮን ልጅ በሆነው በኢታማር ኀላፊነት ነበር። 9በእነርሱ ኀላፊነት የሚጠበቁት ንዋያተ ቅድሳት በትከሻቸው የሚሸከሙአቸው ስለ ሆኑ ሙሴ ለቀዓታውያን ሠረገሎችንም ሆነ በሬዎችን አልሰጣቸውም።
10መሠዊያው በተባረከበት ቀን መሪዎቹ መሠዊያውን ለመቀደስ በመሠዊያው ፊት ቊርባን አቀረቡ። 11እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በዐሥራ ሁለት ተከታታይ ቀኖች ውስጥ በእያንዳንዱ ቀን ከዐሥራ ሁለቱ አለቆች አንዱ መሠዊያው ለሚቀደስበት ክብረ በዓል የሚሆን መባ ያቀርቡ ዘንድ ንገራቸው።”
12በመጀመሪያው ቀን መባውን ያቀረበው ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ፤ 13ያቀረባቸውም መባዎች እነዚህ ናቸው፦ በመቅደሱ ሚዛን መሠረት መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን አንድ ከብር የተሠራ ዝርግ ሳሕን፥ ከሰባ ሰቅል ብር የተሠራ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፥ ሁለቱም ለእህል ቊርባን በሚሆን ከዘይት ጋር በተቀላቀለ ደቃቅ ዱቄት የተሞሉ፥ 14ዕጣን የተሞላበት አንድ ከወርቅ የተሠራ ዐሥር ሰቅል የዕጣን መያዣ፥ 15ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ አንድ ዓመት የሆነው ጠቦት፥ 16አንድ ተባት ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት 17ለአንድነት መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው፥ አምስት ተባት ፍየሎችና አምስት ተባት በጎች ይህ የአሚናዳብ ልጅ የነአሶን መባ ነበረ።
የሚከተሉት ሌሎቹም ልክ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ያቀረበውን ዝርዝር አቅርበዋል።
18-23በሁለተኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከይሳኮር ነገድ የጹዓር ልጅ ናትናኤል ነበር።
24-29በሦስተኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከዛብሎን ነገድ የሔሎን ልጅ ኤሊአብ ነበር። 30-35በአራተኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከሮቤል ነገድ የሰድዩር ልጅ ኤልጹር ነበር።
36-40በአምስተኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከስምዖን ነገድ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል ነበር።
41-47በስድስተኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከጋድ ነገድ የራጉኤል ልጅ ኤልያሳፍ ነበር።
48-53በሰባተኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከኤፍሬም ነገድ የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማዕ ነበር።
54-59በስምንተኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከምናሴ ነገድ የፍዳጹር ልጅ ገማልኤል ነበር።
60-65በዘጠነኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከብንያም ነገድ የጊዳዖኒ ልጅ አቢዳን ነበር።
66-71በዐሥረኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከዳን ነገድ የዓሚሻዳይ ልጅ አኪዔዜር ነበር።
72-77በዐሥራ አንደኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከአሴር ነገድ የኤክራን ልጅ ፋግዔል ነበር። 78-83በዐሥራ ሁለተኛው ቀን መባውን ያቀረበው ከንፍታሌም ነገድ የዔናን ልጅ አሒራዕ ነበር።
84መሠዊያው በተቀባ ቀን መሠዊያው እንዲቀደስበት ያቀረቡት መባ ይህ ነበር፦ ዐሥራ ሁለት ከብር የተሠሩ ዝርግ ሳሕኖች፥ ዐሥራ ሁለት ከብር የተሠሩ ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ ዐሥራ ሁለት ከወርቅ የተሠሩ የዕጣን ማስቀመጫዎች፥ 85በመቅደሱ ሚዛን መሠረት እያንዳንዱ የብር ዝርግ ሳሕን መቶ ሠላሳ ሰቅል፥ እያንዳንዱ ጐድጓዳ ሳሕን ሰባ ሰቅል፥ እነዚህ ሁሉ ከብር የተሠሩት ዕቃዎች በመቅደሱ ሚዛን መሠረት ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ይመዝኑ ነበር፤ 86ዐሥራ ሁለቱ ከወርቅ የተሠሩት የዕጣን ማስቀመጫዎች በመቅደሱ ሚዛን መሠረት እያንዳንዳቸው ዐሥር ሰቅል የሚመዝኑ ሲሆኑ በጠቅላላው አንድ መቶ ኻያ ሰቅል ይመዝኑ ነበር። 87ለሚቃጠል መሥዋዕት የቀረበው የከብት ብዛት ዐሥራ ሁለት ኰርማዎች፥ ዐሥራ ሁለት አውራ በጎች፥ ባለ አንድ ዓመት ዕድሜ የሆኑ ዐሥራ ሁለት ተባት በጎች ከእህል ቊርባናቸው ጋርና ዐሥራ ሁለት ተባት ፍየሎች ለኃጢአት መሥዋዕት፥ 88ለአንድነት መሥዋዕት የቀረቡት የከብት ብዛት፦ ኻያ አራት ኰርማዎች፥ ሥልሳ አውራ በጎች፥ ሥልሳ ተባት ፍየሎች፥ ባለ አንድ ዓመት ዕድሜ ሥልሳ ተባት በጎች፥ መሠዊያው ከተቀባ በኋላ ለመቅደስ የቀረበ ቊርባን ይህ ነው።
89ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወደ መገናኛው ድንኳን በገባ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በኪሩቤል መካከል ካለው ከቃል ኪዳኑ ታቦት መክደኛ በላይ ሆኖ ሲናገረው ሰማ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ