ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም መጡ፤ ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፦ “በመንገድ ሳላችሁ የተከራከራችሁበት ነገር ምን ነበር?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ዝም አሉ፤ ይህም በመንገድ ሳሉ፥ “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” እያሉ ይከራከሩ ስለ ነበረ ነው። እርሱም ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፥ “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ ማናቸውም ሰው የሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት፤” አላቸው። አንድ ሕፃን አምጥቶ በመካከላቸው አቆመው፤ ዐቅፎትም እንዲህ አላቸው፦ “እንደዚህ ካሉት ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ እኔን ሳይሆን፥ የላከኝን ይቀበላል።” ዮሐንስ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያስወጣ አየን፤ ግን ከእኛም ጋር ስላልሆነ ከለከልነው፤” አለው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “በስሜ ተአምር እያደረገ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ የሚናገር ስለሌለ ተዉት፤ አትከልክሉት፤ እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ አንድ ብርጭቆ ውሃ እንኳ የሚያጠጣቸው ዋጋውን አያጣም፤” አላቸው። “ማንም ሰው በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከትንንሾቹ አንዱን ከሚያስት ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል። ስለዚህ እጅህ ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ ቈርጠህ ጣለው! ሁለት እጅ እያለህ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ ጒንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱ የማይጠፋበት ስፍራ ነው። እግርህም ቢያስትህ፥ ቈርጠህ ጣለው፤ ሁለት እግር እያለህ፥ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ፥ አንካሳ ሆነህ፥ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። [ ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱ የማይጠፋበት ስፍራ ነው።] ዐይንህም ቢያስትህ፥ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን እያለህ፥ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል። ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱም የማይጠፋበት ስፍራ ነው። “መሥዋዕት በጨው እንደሚጠራ እያንዳንዱ ሰው በእሳት መጥራት አለበት። “ጨው መልካም ነው፤ ይሁን እንጂ፥ የጨውነቱን ጣዕም ካጣ በምን ታጣፍጡታላችሁ? “በእናንተም የፍቅር ጨው ጣዕም ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ተስማምታችሁ በሰላም ኑሩ፤” አለ።
የማርቆስ ወንጌል 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 9:33-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos