የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 9:33-50

ማርቆስ 9:33-50 NASV

ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ቤት ከገባ በኋላም፣ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ። ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው። አንድ ሕፃን አምጥቶም በመካከላቸው አቆመ፤ ዐቅፎትም፣ “ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ማንም ቢኖር የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” አላቸው። ዮሐንስም፣ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፣ እኛን ስለማይከተልም ልንከለክለው ሞከርን” አለው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “አትከልክሉት፤ ማንም በስሜ ታምር ሠርቶ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ መናገር አይችልም፤ የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋራ ነውና፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የክርስቶስ በመሆናችሁ በስሜ አንድ ኩባያ ውሃ የሚሰጣችሁ ሁሉ ዋጋውን አያጣም። “ማንም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል። ስለዚህ እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ እሳቱ ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ከመሄድ፣ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤ [በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።] እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ ዐንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤ [በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።] ዐይንህ ብታሰናክልህ ጐልጕለህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤ “ ‘በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።’ ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና። “ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው ጨውነቱን ቢያጣ እንዴት መልሳችሁ ጣዕም እንዲኖረው ታደርጉታላችሁ? ጨው በውስጣችሁ ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች