ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጀልባ በመሳፈር ባሕሩን ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ። በዚያም ሰዎች በአልጋ ላይ የተኛ አንድ ሽባ ይዘው ወደ እርሱ መጡ። እርሱም እምነታቸውን አይቶ፥ ሽባውን፥ “ልጄ ሆይ! አይዞህ፤ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ አንዳንድ የሕግ መምህራን፥ “ይህ ሰው በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ይናገራል!” እያሉ በልባቸው አሰቡ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምን ይህን ክፉ ነገር በልባችሁ ታስባላችሁ? ለመሆኑ ‘ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ” ሽባውን ሰው “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። ሰውዬውም ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተገረሙ፤ እንዲህ ያለውንም ሥልጣን ለሰው በመስጠቱ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ተነሥቶ ሲሄድ ሳለ ማቴዎስ የተባለውን ቀራጭ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ!” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች፥ ወደዚያ መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማእድ ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም ይህን አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ስለምን አብሮ ይበላል?” አሉአቸው። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም። ሂዱ፤ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ ተብሎ የተጻፈው ምን ማለት እንደ ሆነ መርምራችሁ አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው” አላቸው። በዚያን ጊዜ፥ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ መጥተው፥ “እኛና ፈሪሳውያን ዘወትር እንጾማለን፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎች ማዘን ይገባቸዋልን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ ዕራፊ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ቢጣፍ ግን አዲሱ ዕራፊ አሮጌውን ልብስ ቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል። እንዲሁም በአረጀ የውሃ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ተበላሽቶ ከጥቅም ውጪ ይሆናል። ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፤ በዚህም ዐይነት፥ ሁለቱም በደኅና ተጠብቀው ይኖራሉ።” ኢየሱስ ይህን ሲነግራቸው ሳለ፥ አንድ የምኲራብ አለቃ ወደ እርሱ መጣ፤ በግንባሩም በኢየሱስ ፊት ተደፍቶ፥ “እነሆ፥ ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ ነገር ግን አንተ መጥተህ እጅህን ብትጭንባት ትድናለች” አለው። ኢየሱስም ተነሣና ሰውየውን ተከትሎ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረው ሄዱ።
የማቴዎስ ወንጌል 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 9:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች