ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ባሕሩን በጀልባ ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ። በዚያም ሰዎች አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አይዞህ አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን፣ “ይህማ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው” በማለት በልባቸው አጕረመረሙ። ኢየሱስ ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ አለ፤ “ክፉ ነገር በልባችሁ ለምን ታስባላችሁ? ለመሆኑ፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀልላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው” ብሎ፣ ሽባውን፣ “ተነሣ! ቃሬዛህን ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። ሽባውም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተደነቁ፤ በፍርሀት ተሞልተው፣ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ መሰብሰቢያው ተቀምጦ አየና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው። ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ላይ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ዐብረው ሊመገቡ ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋራ ለምን ዐብሮ ይበላል?” ብለው ጠየቋቸው። ኢየሱስም የተናገሩትን ሰምቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሐኪም የሚያስፈልገው ለሕመምተኞች እንጂ ለጤነኞች አይደለም፤ ሄዳችሁ፣ ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ፤’ የሚለውን ቃል ትርጕም አጢኑ፤ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና።” የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛና ፈሪሳውያን ስንጾም፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን አይጾሙም?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ዐብሯቸው እያለ ዕድምተኞቹ እንዴት ሊያዝኑ ይችላሉ? ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያም ጊዜ ይጾማሉ። “በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ቍራጭ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም፤ ይህ ከሆነ አዲሱ ዕራፊ ካረጀው ልብስ ላይ ተቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል። አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ ማንም አያስቀምጥም፤ ይህ ከሆነ አቍማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ ይጨመራል፤ በዚህ ሁኔታ የወይን ጠጁና አቍማዳው በደኅና ተጠብቀው ይቈያሉ።” ኢየሱስ ሰዎቹን በማናገር ላይ ሳለ፣ አንድ የምኵራብ አለቃ መጥቶ ከፊቱ ተደፍቶ፣ “ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው። ኢየሱስም ተነሥቶ ዐብሮት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
ማቴዎስ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 9:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች