የማቴዎስ ወንጌል 9
9
ኢየሱስ ሽባውን ሰው እንደ ፈወሰ
(ማር. 2፥1-12፤ ሉቃ. 5፥17-26)
1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጀልባ በመሳፈር ባሕሩን ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ። 2በዚያም ሰዎች በአልጋ ላይ የተኛ አንድ ሽባ ይዘው ወደ እርሱ መጡ። እርሱም እምነታቸውን አይቶ፥ ሽባውን፥ “ልጄ ሆይ! አይዞህ፤ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው። 3በዚህ ጊዜ አንዳንድ የሕግ መምህራን፥ “ይህ ሰው በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ይናገራል!” እያሉ በልባቸው አሰቡ። 4ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምን ይህን ክፉ ነገር በልባችሁ ታስባላችሁ? 5ለመሆኑ ‘ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? 6ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ” ሽባውን ሰው “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። 7ሰውዬውም ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። 8ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተገረሙ፤ እንዲህ ያለውንም ሥልጣን ለሰው በመስጠቱ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
ኢየሱስ ማቴዎስ የተባለውን ሌዊን መጥራቱ
(ማር. 2፥13-17፤ ሉቃ. 5፥27-32)
9ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ተነሥቶ ሲሄድ ሳለ ማቴዎስ የተባለውን ቀራጭ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ!” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።
10ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች፥ ወደዚያ መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማእድ ተቀመጡ። 11ፈሪሳውያንም ይህን አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ስለምን አብሮ ይበላል?” አሉአቸው። #15፥1-2። 12ኢየሱስም ይህን ሰምቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም። 13ሂዱ፤ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ ተብሎ የተጻፈው ምን ማለት እንደ ሆነ መርምራችሁ አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው” አላቸው። #ሆሴዕ 6፥6፤ ማቴ. 12፥7።
ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 2፥18-22፤ ሉቃ. 5፥33-39)
14በዚያን ጊዜ፥ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ መጥተው፥ “እኛና ፈሪሳውያን ዘወትር እንጾማለን፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 15እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎች ማዘን ይገባቸዋልን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። 16በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ ዕራፊ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ቢጣፍ ግን አዲሱ ዕራፊ አሮጌውን ልብስ ቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል። 17እንዲሁም በአረጀ የውሃ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ተበላሽቶ ከጥቅም ውጪ ይሆናል። ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፤ በዚህም ዐይነት፥ ሁለቱም በደኅና ተጠብቀው ይኖራሉ።”
ስለ ኢያኢሮስ ልጅና የኢየሱስን ልብስ ስለ ነካች ሴት
(ማር. 5፥21-43፤ ሉቃ. 8፥40-56)
18ኢየሱስ ይህን ሲነግራቸው ሳለ፥ አንድ የምኲራብ አለቃ ወደ እርሱ መጣ፤ በግንባሩም በኢየሱስ ፊት ተደፍቶ፥ “እነሆ፥ ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ ነገር ግን አንተ መጥተህ እጅህን ብትጭንባት ትድናለች” አለው። 19ኢየሱስም ተነሣና ሰውየውን ተከትሎ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረው ሄዱ።
20እነሆ፥ ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየመታት ትሠቃይ የነበረች አንዲት ሴት፥ በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ በስተኋላ መጥታ የልብሱን ጫፍ በእጅዋ ነካች። #ዘኍ. 15፥38፤ ዘዳ. 22፥12። 21ይህንንም ያደረገችው “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ በልብዋ አስባ ስለ ነበር ነው። 22ኢየሱስም መለስ ብሎ አያትና “አይዞሽ ልጄ ሆይ! እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴትዮዋም ወዲያውኑ ዳነች።
23ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ምኲራብ አለቃው ቤት በደረሰ ጊዜ የሐዘን እምቢልታ ነፊዎችንና እየተራወጡ በመጮኽ የሚያለቅሱትን ሰዎች አየ። 24እርሱም “ሁላችሁም ከዚህ ውጡ! ልጅትዋ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞተችም!” አላቸው። እነርሱ ግን በማፌዝ ሳቁበት። 25ሰዎቹም ከወጡ በኋላ፥ ኢየሱስ ልጅትዋ ወደምትገኝበት ክፍል ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ እርሷም ተነሣች። 26የዚህም ነገር ዝና በዚያ አገር ሁሉ ተሰማ።
ኢየሱስ ሁለት ዐይነ ስውሮችን እንደአዳነ
27ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ተነሥቶ ሲሄድ ሁለት ዕውሮች ተከተሉት፤ እነርሱም “የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ ይጮኹ ነበር። 28ኢየሱስ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም “እኔ ይህን ማድረግ እንደምችል ታምናላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎ፥ ጌታ ሆይ!” ሲሉ መለሱ። 29ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ዐይኖቻቸውን በእጁ ዳሰሰና፦ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ!” አላቸው። 30ዐይኖቻቸውም ተከፈቱ፤ ኢየሱስም “ይህን ነገር ለማንም አትንገሩ!” ሲል በጥብቅ አዘዛቸው። 31እነርሱ ግን ሄደው በዚያ አገር ሁሉ ስለ ኢየሱስ ዝና አወሩ።
ኢየሱስ አንድ መናገር የተሳነው ሰው መፈወሱ
32ዐይኖቻቸው የተከፈቱላቸው ሰዎች ወጥተው በሄዱ ጊዜ ሌሎች ሰዎች ጋኔን ያደረበትን አንድ ድዳ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ። 33ጋኔኑም ከእርሱ በወጣ ጊዜ ድዳው ሰው ተናገረ፤ ሕዝቡም “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ከቶ ታይቶ አይታወቅም!” እያሉ ተደነቁ። 34ፈሪሳውያን ግን “እርሱ አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ አማካይነት ነው” አሉ። #ማቴ. 10፥25፤ 12፥34፤ ማር. 3፥22፤ ሉቃ. 11፥15።
ኢየሱስ ለሕዝቡ መራራቱ
35ኢየሱስም በምኲራቦቻቸው እያስተማረ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከ፥ ሕዝቡን ከበሽታና ከደዌ ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተሞችና በመንደሮች ሁሉ ይዘዋወር ነበር። #ማቴ. 4፥23፤ ማር. 1፥39፤ ሉቃ. 4፥44። 36ሕዝቡ ግን እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ባያቸው ጊዜ አዘነላቸው። #ዘኍ. 27፥17፤ 1ነገ. 22፥17፤ 2ዜ.መ. 18፥16፤ ሕዝ. 34፥5፤ ዘካ. 10፥2፤ ማር. 6፥34። 37ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው። 38እንግዲህ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ሥራ እንዲልክ የመከሩን ጌታ ለምኑት።” #ሉቃ. 10፥2።
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997