የማቴዎስ ወንጌል 26:1-46

የማቴዎስ ወንጌል 26:1-46 አማ05

ኢየሱስ ይህን ሁሉ ትምህርት አስተምሮ ባበቃ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከሁለት ቀን በኋላ የፋሲካ በዓል እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅ ለመሰቀል ተላልፎ ይሰጣል።” በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች በካህናት አለቃው ግቢ ተሰበሰቡ። እዚያም ኢየሱስን በተንኰል ለመያዝና ለመግደል አሤሩ። ነገር ግን “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” አሉ። እነሆ፥ ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበረ። በዚያም ኢየሱስ በማእድ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ሽቶውንም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን አይተው ተቈጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሽቶ ለምን በከንቱ ባከነ? ይህ ሽቶ በብዙ ዋጋ ተሸጦ ለድኾች ሊሰጥ ይችል ነበር!” ኢየሱስም ይህን ማለታቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እዚህ አልገኝም። እርስዋ ይህን ሽቶ በእኔ ላይ ማፍሰስዋ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው። በእውነት እላችኋለሁ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያዋ ይነገርላታል።” በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው አስቀሮታዊው ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ሄደና “ኢየሱስን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አለ። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ሰጡት እርሱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “የፋሲካ በዓልን ራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “ወደ ከተማው ስትገቡ ወደምታገኙት ሰው ቤት ሂዱና ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በዓል ራት የምበላው በአንተ ቤት ነው ይላል’ በሉት” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ የፋሲካውንም ራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። ሲበሉም ኢየሱስ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” አለ። ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር በጣም አዝነው፥ እያንዳንዳቸው ጌታ ሆይ፥ “እኔ እሆን?” እያሉ ይጠይቁት ጀመር። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ከእኔ ጋር በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰው ልጅን አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፥ “መምህር ሆይ! እኔ እሆን?” አለ። ኢየሱስም፥ “አንተ እንዳልከው ነው” አለው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ እንዲህ ሲል ሰጣቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጽዋ ጠጡ፤ ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ፤” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና በዚህች ሌሊት፥ ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ። ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም!” ብሎ ተናገረ። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮሁ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልግ ቢሆን እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” አለው። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንዲሁ ይሉ ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሱ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ሄጄ እስክጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ” አላቸው። ከእርሱ ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች አስከትሎ ሄደ፤ ያዝንና ይጨነቅም ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ለመሞት እስክደርስ ድረስ አዝኛለሁ፤ እናንተ እዚህ ቈዩ፤ ከእኔም ጋር ንቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደና፥ በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፥ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ጽዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” ከዚህ በኋላ ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ፥ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር ለአንዲት ሰዓት እንኳ መንቃት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ርቆ ሄደና “አባቴ ሆይ! ይህ የመከራ ጽዋ ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ የአንተ ፈቃድ ይሁን” ሲል ጸለየ። ደግሞም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። እንደገናም ትቶአቸው ሄደና ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ መጣና እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? ዕረፍትም እያደረጋችሁ ነውን? እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ የሚሰጥበት ሰዓቱ ደርሶአል፤ ተነሡ እንሂድ! እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል!”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች