ማቴዎስ 26:1-46

ማቴዎስ 26:1-46 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል ዐልፎ ይሰጣል” አላቸው። ከዚህ በኋላ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በተባለ ሊቀ ካህን ግቢ ውስጥ ተሰብስበው፤ በረቀቀ መንገድ ኢየሱስን ለማስያዝና ለማስገደል ተማከሩ። ነገር ግን፣ “በሕዝቡ መካከል ረብሻ እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” በማለት ተስማሙ። ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ አንድ ብልቃጥ የአልባስጥሮስ ሽቱ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማእድ ላይ ተቀምጦ ሳለም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን በተመለከቱ ጊዜ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ሽቱው በብዙ ዋጋ ተሸጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ሲቻል!” ኢየሱስ ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች፤ ድኾች ምን ጊዜም ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ አልሆንም። ሽቱውን በሰውነቴ ላይ ማፍሰሷ፣ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በየትኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቧልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን እራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ በማእድ ተቀመጠ፤ በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም እጅግ ዐዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋራ እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤ የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው። እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው። እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “ዕንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋራ በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከአሁን ጀምሮ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም በዚህች ሌሊት በእኔ ተሰናክላችሁ ትሄዳላችሁ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ።’ ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም መልሶ፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ በፍጹም አልሰናከልም” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዛሬዋ ሌሊት ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋራ መሞት ቢያስፈልግ እንኳ ከቶ አልክድህም!” አለው። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት በሙሉ እንደዚሁ አሉ። ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እነርሱንም፣ “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ከርሱም ጋራ ጴጥሮስን እና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር፤ ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዝናለች፤ እዚሁ ሁኑና ከእኔ ጋራ ነቅታችሁ ቈዩ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ። ከዚያም ተመልሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፤ ከእኔ ጋራ ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ። እንደ ገናም በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር ተኝተው አገኛቸው። ትቷቸውም እንደ ገና በመሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ቀደም ብሎ የጸለየውን ጸሎት ደገመ። ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? እነሆ፤ ሰዓቱ ቀርቧል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”

ማቴዎስ 26:1-46 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢየሱስም እነዚህን ቃሎች ሁሉ በፈጸመ ጊዜ፥ ለደቀ መዛሙርቱ “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል፤” አለ። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤ ነገር ግን “በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን፤” አሉ። ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቈጡና “ይህ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና፤” አሉ። ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው “መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርስዋ ይህን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።” በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ “ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ?” እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ?” አሉት። እርሱም “ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል’ በሉት፤” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል፤” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ “ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር፤” አለ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ፤” አለው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤” አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፤ “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣም።” መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ፤’ የሚል ተጽፎአልና፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ፤” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። ጴጥሮስም “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም፤” አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ፤” አላቸው። ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ፤” አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ “አባቴ! ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን፤” አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን “እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አለው። ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና “አባቴ! ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን፤” አለ። ደግሞም መጥቶ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፤ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ። ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ “እንግዲህስ ተኙ፤ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል፤” አላቸው።

ማቴዎስ 26:1-46 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል ዐልፎ ይሰጣል” አላቸው። ከዚህ በኋላ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በተባለ ሊቀ ካህን ግቢ ውስጥ ተሰብስበው፤ በረቀቀ መንገድ ኢየሱስን ለማስያዝና ለማስገደል ተማከሩ። ነገር ግን፣ “በሕዝቡ መካከል ረብሻ እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” በማለት ተስማሙ። ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ አንድ ብልቃጥ የአልባስጥሮስ ሽቱ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማእድ ላይ ተቀምጦ ሳለም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን በተመለከቱ ጊዜ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ሽቱው በብዙ ዋጋ ተሸጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ሲቻል!” ኢየሱስ ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች፤ ድኾች ምን ጊዜም ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ አልሆንም። ሽቱውን በሰውነቴ ላይ ማፍሰሷ፣ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በየትኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቧልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን እራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ በማእድ ተቀመጠ፤ በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም እጅግ ዐዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋራ እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤ የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው። እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው። እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “ዕንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋራ በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከአሁን ጀምሮ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም በዚህች ሌሊት በእኔ ተሰናክላችሁ ትሄዳላችሁ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ።’ ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም መልሶ፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ በፍጹም አልሰናከልም” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዛሬዋ ሌሊት ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋራ መሞት ቢያስፈልግ እንኳ ከቶ አልክድህም!” አለው። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት በሙሉ እንደዚሁ አሉ። ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እነርሱንም፣ “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ከርሱም ጋራ ጴጥሮስን እና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር፤ ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዝናለች፤ እዚሁ ሁኑና ከእኔ ጋራ ነቅታችሁ ቈዩ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ። ከዚያም ተመልሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፤ ከእኔ ጋራ ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ። እንደ ገናም በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር ተኝተው አገኛቸው። ትቷቸውም እንደ ገና በመሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ቀደም ብሎ የጸለየውን ጸሎት ደገመ። ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? እነሆ፤ ሰዓቱ ቀርቧል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”

ማቴዎስ 26:1-46 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም እነዚህን ቃሎች ሁሉ በፈጸመ ጊዜ፥ ለደቀ መዛሙርቱ፦ ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ፥ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል አለ። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥ ኢየሱስንም በተንኵኦል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤ ነገር ግን፦ በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን አሉ። ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቍኦጡና፦ ይህ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና አሉ። ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርስዋ ይህን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል። በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፦ ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት። እርሱም፦ ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ፦ መምህር፦ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ፦ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቍኦርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፦ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው። ኢየሱስ፦ እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። ጴጥሮስ፦ ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን፦ እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና፦ አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ። ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፥ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ። ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ፦ እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።

ማቴዎስ 26:1-46 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ይህን ሁሉ ትምህርት አስተምሮ ባበቃ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከሁለት ቀን በኋላ የፋሲካ በዓል እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅ ለመሰቀል ተላልፎ ይሰጣል።” በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች በካህናት አለቃው ግቢ ተሰበሰቡ። እዚያም ኢየሱስን በተንኰል ለመያዝና ለመግደል አሤሩ። ነገር ግን “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” አሉ። እነሆ፥ ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበረ። በዚያም ኢየሱስ በማእድ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ሽቶውንም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን አይተው ተቈጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሽቶ ለምን በከንቱ ባከነ? ይህ ሽቶ በብዙ ዋጋ ተሸጦ ለድኾች ሊሰጥ ይችል ነበር!” ኢየሱስም ይህን ማለታቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እዚህ አልገኝም። እርስዋ ይህን ሽቶ በእኔ ላይ ማፍሰስዋ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው። በእውነት እላችኋለሁ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያዋ ይነገርላታል።” በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው አስቀሮታዊው ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ሄደና “ኢየሱስን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አለ። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ሰጡት እርሱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “የፋሲካ በዓልን ራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “ወደ ከተማው ስትገቡ ወደምታገኙት ሰው ቤት ሂዱና ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በዓል ራት የምበላው በአንተ ቤት ነው ይላል’ በሉት” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ የፋሲካውንም ራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። ሲበሉም ኢየሱስ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” አለ። ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር በጣም አዝነው፥ እያንዳንዳቸው ጌታ ሆይ፥ “እኔ እሆን?” እያሉ ይጠይቁት ጀመር። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ከእኔ ጋር በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰው ልጅን አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፥ “መምህር ሆይ! እኔ እሆን?” አለ። ኢየሱስም፥ “አንተ እንዳልከው ነው” አለው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ እንዲህ ሲል ሰጣቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጽዋ ጠጡ፤ ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ፤” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና በዚህች ሌሊት፥ ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ። ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም!” ብሎ ተናገረ። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮሁ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልግ ቢሆን እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” አለው። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንዲሁ ይሉ ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሱ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ሄጄ እስክጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ” አላቸው። ከእርሱ ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች አስከትሎ ሄደ፤ ያዝንና ይጨነቅም ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ለመሞት እስክደርስ ድረስ አዝኛለሁ፤ እናንተ እዚህ ቈዩ፤ ከእኔም ጋር ንቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደና፥ በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፥ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ጽዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” ከዚህ በኋላ ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ፥ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር ለአንዲት ሰዓት እንኳ መንቃት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ርቆ ሄደና “አባቴ ሆይ! ይህ የመከራ ጽዋ ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ የአንተ ፈቃድ ይሁን” ሲል ጸለየ። ደግሞም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። እንደገናም ትቶአቸው ሄደና ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ መጣና እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? ዕረፍትም እያደረጋችሁ ነውን? እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ የሚሰጥበት ሰዓቱ ደርሶአል፤ ተነሡ እንሂድ! እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል!”

ማቴዎስ 26:1-46 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንዲህም ሆነ፤ ኢየሱስ እነዚህን ቃሎች ሁሉ ተናግሮ ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል ተላልፎ ይሰጣል።” በዚያን ጊዜ ሊቃነ ካህናትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህኑ ግቢ ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስን በተንኰል ይዘው ሊገድሉት ተማከሩ፤ ነገር ግን “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” አሉ። ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ በማዕድም ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በራሱ ላይም አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቆጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና።” ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው “ይህችን ሴት ለምን ታስጨንቁአታላችሁ? ለእኔ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ይህን ሽቶ በሰውነቴ ላይ በማፍሰስ ለቀብሬ አደረገችው። እውነት እላችኋለሁ ይህ የምሥራች በሚሰበክበት በመላው ዓለም፥ ይህ እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለመታሰቢያዋ ይነገራል።” በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ እንዲህ አላቸው “አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ ምን ትሰጡኛላችሁ?” እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አለ “ወደ ከተማ ወደ አንድ ሰው ሄዳችሁ ‘መምህሩ እንዲህ ይላል፥ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በአንተ ቤት አደርጋለሁ ይላል’ በሉት።” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካውንም አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም ሳሉ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዳቸው “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከእኔ ጋር እጁን በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠልቀው፥ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ” አለው። ሲበሉም ሳሉ ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አለ። ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህ ብሎ ሰጣቸው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳን ደሜ ይህ ነው። በአባቴ መንግሥት አዲሱን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ ከዚህ ወይን አልጠጣም እላችኋለሁ።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና፥ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም “ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ፥ ከቶ አልክድህም፤” አለው። ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ እንደዚሁ አሉ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች ይዞ ሄደና ማዘንና መጨነቅ ጀመረ። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ እዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው። ወደ ፊት ጥቂት እልፍ ብሎ በፊቱ ተደፋና እንዲህ ሲል ጸለየ “አባቴ! የሚቻል ከሆነ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ አይሁን።” ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፥ ጸልዩም፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ “አባቴ ሆይ! ይህንን ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ፥ ፈቃድህ ይሁን” ብሎ ጸለየ። ዳግመኛ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና። እንደገና ትቶአቸው ሄደ፤ ያንኑ ቃል ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጥቶ እንዲህ አላቸው “ከእንግዲህስ ተኙ፥ ዕረፉም፤ እነሆ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።”