ማቴዎስ 26:1-46

ማቴዎስ 26:1-46 NASV

ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል ዐልፎ ይሰጣል” አላቸው። ከዚህ በኋላ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በተባለ ሊቀ ካህን ግቢ ውስጥ ተሰብስበው፤ በረቀቀ መንገድ ኢየሱስን ለማስያዝና ለማስገደል ተማከሩ። ነገር ግን፣ “በሕዝቡ መካከል ረብሻ እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” በማለት ተስማሙ። ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ አንድ ብልቃጥ የአልባስጥሮስ ሽቱ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማእድ ላይ ተቀምጦ ሳለም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን በተመለከቱ ጊዜ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ሽቱው በብዙ ዋጋ ተሸጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ሲቻል!” ኢየሱስ ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች፤ ድኾች ምን ጊዜም ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ አልሆንም። ሽቱውን በሰውነቴ ላይ ማፍሰሷ፣ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በየትኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቧልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን እራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ በማእድ ተቀመጠ፤ በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም እጅግ ዐዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋራ እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤ የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው። እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው። እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “ዕንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋራ በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከአሁን ጀምሮ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም በዚህች ሌሊት በእኔ ተሰናክላችሁ ትሄዳላችሁ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ።’ ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም መልሶ፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ በፍጹም አልሰናከልም” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዛሬዋ ሌሊት ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋራ መሞት ቢያስፈልግ እንኳ ከቶ አልክድህም!” አለው። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት በሙሉ እንደዚሁ አሉ። ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እነርሱንም፣ “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ከርሱም ጋራ ጴጥሮስን እና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር፤ ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዝናለች፤ እዚሁ ሁኑና ከእኔ ጋራ ነቅታችሁ ቈዩ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ። ከዚያም ተመልሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፤ ከእኔ ጋራ ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ። እንደ ገናም በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር ተኝተው አገኛቸው። ትቷቸውም እንደ ገና በመሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ቀደም ብሎ የጸለየውን ጸሎት ደገመ። ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? እነሆ፤ ሰዓቱ ቀርቧል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች