ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ማዶ በተሻገሩ ጊዜ ረስተው እንጀራ አልያዙም ነበር፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ልብ አድርጉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ” አላቸው። እነርሱም “ይህን ማለቱ ምናልባት እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” በማለት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ! ‘እንጀራ ስላልያዝን ነው’ ብላችሁ ስለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና የማታስተውሉ ናችሁን? አምስት እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባት እንጀራ ለአራት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንግዲህ ‘ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ!’ ብዬ ስነግራችሁ ስለ እንጀራ አለመሆኑን እንዴት አታስተውሉም?” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ተጠንቀቁ ያላቸው ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዳልሆነ ተገነዘቡ። ኢየሱስ የፊልጶስ ቂሳርያ ወደሚባል ክፍለ ሀገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶች ‘መጥምቁ ዮሐንስ ነው’ ይላሉ፤ ሌሎች ‘ኤልያስ ነው’ ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ‘ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው’ ይላሉ” አሉት። ኢየሱስም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። በዚያን ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፦ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! የተባረክህ ነህ! ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሰው አይደለም። እኔም እንዲህ እልሃለሁ፤ አንተ (ጴጥሮስ)፥ አለት ነህ፤ በዚህችም የመሠረት ድንጋይ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ ይህችንም ቤተ ክርስቲያን የሞት ኀይል እንኳ አያሸንፋትም። እነሆ፥ ለአንተ የሰማይ መንግሥትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።”
የማቴዎስ ወንጌል 16 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 16:5-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos