ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር። ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እርስ በርሳችሁ፣ እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? ዐምስቱ እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን? ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው። ኢየሱስ ፊልጶስ ቂሳርያ ወደተባለው ግዛት በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለመሆኑ ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይላሉ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። እርሱም፣ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ምስጉን ነህ፤ ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም። አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አያሸንፏትም። የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርኸው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታኸው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።”
ማቴዎስ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 16
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 16:5-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos