ማቴዎስ 16:5-19
ማቴዎስ 16:5-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ፤” አላቸው። እነርሱም “እንጀራ ባንይዝ ነው፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም?” እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ። ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?” ብሎ ጠየቀ። እነርሱም “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው፤” ይላሉ አሉት። እርሱም “እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፤ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚችም ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።”
ማቴዎስ 16:5-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር። ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እርስ በርሳችሁ፣ እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? ዐምስቱ እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን? ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው። ኢየሱስ ፊልጶስ ቂሳርያ ወደተባለው ግዛት በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለመሆኑ ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይላሉ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። እርሱም፣ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ምስጉን ነህ፤ ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም። አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አያሸንፏትም። የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርኸው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታኸው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።”
ማቴዎስ 16:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ። ኢየሱስም፦ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው። እነርሱም፦ እንጀራ ባንይዝ ነው ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ እምነት የጕኦደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን? እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ። ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።
ማቴዎስ 16:5-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ማዶ በተሻገሩ ጊዜ ረስተው እንጀራ አልያዙም ነበር፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ልብ አድርጉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ” አላቸው። እነርሱም “ይህን ማለቱ ምናልባት እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” በማለት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ! ‘እንጀራ ስላልያዝን ነው’ ብላችሁ ስለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና የማታስተውሉ ናችሁን? አምስት እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባት እንጀራ ለአራት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንግዲህ ‘ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ!’ ብዬ ስነግራችሁ ስለ እንጀራ አለመሆኑን እንዴት አታስተውሉም?” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ተጠንቀቁ ያላቸው ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዳልሆነ ተገነዘቡ። ኢየሱስ የፊልጶስ ቂሳርያ ወደሚባል ክፍለ ሀገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶች ‘መጥምቁ ዮሐንስ ነው’ ይላሉ፤ ሌሎች ‘ኤልያስ ነው’ ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ‘ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው’ ይላሉ” አሉት። ኢየሱስም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። በዚያን ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፦ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! የተባረክህ ነህ! ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሰው አይደለም። እኔም እንዲህ እልሃለሁ፤ አንተ (ጴጥሮስ)፥ አለት ነህ፤ በዚህችም የመሠረት ድንጋይ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ ይህችንም ቤተ ክርስቲያን የሞት ኀይል እንኳ አያሸንፋትም። እነሆ፥ ለአንተ የሰማይ መንግሥትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።”
ማቴዎስ 16:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደቀመዛሙርቱ ወደ ማዶ በሚሻገሩበት ጊዜ እንጀራ መያዝን ረስተው ነበር። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ብለው አሰቡ። ኢየሱስም ይህንን አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስላልያዛችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? አሁንም አታስተውሉምን? አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺህ በቅቶ ስንት መሶብ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺህ በቅቶ ስንት ቅርጫት እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ።” ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠነቀቁ እንዳልነገራቸው ተገነዘቡ። ኢየሱስ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ወደሚባል አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎች ኤልያስ፥ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። እርሱም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! የተባረክህ ነህ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፤ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚችም ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይነግሱባትም። የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው በሰማያት የተፈታ ይሆናል።”