የማቴዎስ ወንጌል 10:24-42

የማቴዎስ ወንጌል 10:24-42 አማ05

ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ አገልጋይም ከጌታው አይበልጥም። ስለዚህ ተማሪ እንደአስተማሪው፥ አገልጋይም እንደ ጌታው ከሆነ ይበቃዋል። የቤቱን ጌታ ‘ብዔልዜቡል’ ብለው ከጠሩት ቤተሰቦቹንማ ከዚህ በከፋ ስም እንዴት አይጠሩአቸውም! “እንግዲህ ሰዎችን አትፍሩ፤ የተሸፈነ መገለጡ አይቀርም፤ የተሰወረም መታወቁ አይቀርም። ስለዚህ እኔ በጨለማ የምነግራችሁን፥ እናንተ በብርሃን ተናገሩት፤ በሹክሹክታ የሰማችሁትንም በከፍተኛ ቦታ ላይ መጥታችሁ በይፋ አስተምሩ። ሥጋን ከመግደል አልፈው ነፍስን መግደል የማይችሉትን ሰዎች አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን አምላክ ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ፥ የሰማይ አባታችሁ ሳይፈቅድ፥ አንዲቱ ድንቢጥ እንኳ በምድር ላይ ወድቃ አትቀርም። የእናንተ ግን የራስ ጠጒራችሁ እንኳ የተቈጠረ ነው። እንግዲህ እናንተ ግን ከብዙ ድንቢጦች እጅግ ስለምትበልጡ ከቶ አትፍሩ። “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ። በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔም በሰማይ አባቴ ፊት እክደዋለሁ። እኔ የመጣሁት፥ ሰላምን በምድር ላይ ለማምጣት አይምሰላችሁ፤ እኔ ጦርነትን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። እኔ የመጣሁት፥ ወንድ ልጅን በአባቱ ላይ፥ ሴት ልጅን በእናትዋ ላይ፥ ምራትን በዐማትዋ ላይ፥ በጠላትነት ለማስነሣት ነው። ስለዚህ የሰው ጠላቶቹ፥ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ፥ የእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ፥ የእኔ ሊሆን አይገባውም። የገዛ ራሱን መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ሰው የእኔ ሊሆን አይገባውም። ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን አብን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል። በእውነት እላችኋለሁ፤ የእኔ ደቀ መዝሙር በመሆኑ፥ ከነዚህ ታናናሾች ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ የሚሰጥ ሰው ዋጋውን አያጣም።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች