ማቴዎስ 10:24-42
ማቴዎስ 10:24-42 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም። ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው! “እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና። በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ። ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቍኦጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ። “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፤ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል። “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።”
ማቴዎስ 10:24-42 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፣ ሎሌም ከጌታው አይበልጥም፤ ደቀ መዝሙር መምህሩን፣ ሎሌም ጌታውን ከመሰለ ይበቃዋል። ባለቤቱን ‘ብዔልዜቡል’ ካሉት፣ ቤተ ሰዎቹንማ እንዴት አብልጠው አይሏቸውም! “ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ መገለጡ፣ የተደበቀ መውጣቱ አይቀርምና። በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን አውሩት፤ በጆሯችሁ የሰማችሁትን በአደባባይ ዐውጁት፤ ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ። በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም። የራስ ጠጕራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው። ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው። “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ ነገር ግን በሰው ፊት የሚክደኝን፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ። “እኔ የመጣሁት ሰላምን በምድር ለማስፈን አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማውረድ አልመጣሁም። እኔ የመጣሁት “ ‘ልጅን ከአባት፣ ሴት ልጅን ከእናቷ ምራትንም ከዐማቷ ለመለያየት ነው፤ የሰው ጠላቶቹ፣ የገዛ ቤተ ሰዎቹ ይሆናሉ።’ “ከእኔ ይልቅ እናቱን ወይም አባቱን የሚወድድ ለእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድድ ለእኔ ሊሆን አይገባም። መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም። ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያገኛታል። “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ያገኛል። ስለዚህ እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ከእነዚህ ከታናናሾች ለአንዱ ደቀ መዝሙሬ በመሆኑ አንድ ጽዋ ቀዝቃዛ ውሃ ቢሰጠው ዋጋውን አያጣም።”
ማቴዎስ 10:24-42 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም። ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው! እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና። በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ። ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቍኦጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ። በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል። እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።
ማቴዎስ 10:24-42 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ አገልጋይም ከጌታው አይበልጥም። ስለዚህ ተማሪ እንደአስተማሪው፥ አገልጋይም እንደ ጌታው ከሆነ ይበቃዋል። የቤቱን ጌታ ‘ብዔልዜቡል’ ብለው ከጠሩት ቤተሰቦቹንማ ከዚህ በከፋ ስም እንዴት አይጠሩአቸውም! “እንግዲህ ሰዎችን አትፍሩ፤ የተሸፈነ መገለጡ አይቀርም፤ የተሰወረም መታወቁ አይቀርም። ስለዚህ እኔ በጨለማ የምነግራችሁን፥ እናንተ በብርሃን ተናገሩት፤ በሹክሹክታ የሰማችሁትንም በከፍተኛ ቦታ ላይ መጥታችሁ በይፋ አስተምሩ። ሥጋን ከመግደል አልፈው ነፍስን መግደል የማይችሉትን ሰዎች አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን አምላክ ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ፥ የሰማይ አባታችሁ ሳይፈቅድ፥ አንዲቱ ድንቢጥ እንኳ በምድር ላይ ወድቃ አትቀርም። የእናንተ ግን የራስ ጠጒራችሁ እንኳ የተቈጠረ ነው። እንግዲህ እናንተ ግን ከብዙ ድንቢጦች እጅግ ስለምትበልጡ ከቶ አትፍሩ። “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ። በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔም በሰማይ አባቴ ፊት እክደዋለሁ። እኔ የመጣሁት፥ ሰላምን በምድር ላይ ለማምጣት አይምሰላችሁ፤ እኔ ጦርነትን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። እኔ የመጣሁት፥ ወንድ ልጅን በአባቱ ላይ፥ ሴት ልጅን በእናትዋ ላይ፥ ምራትን በዐማትዋ ላይ፥ በጠላትነት ለማስነሣት ነው። ስለዚህ የሰው ጠላቶቹ፥ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ፥ የእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ፥ የእኔ ሊሆን አይገባውም። የገዛ ራሱን መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ሰው የእኔ ሊሆን አይገባውም። ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን አብን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል። በእውነት እላችኋለሁ፤ የእኔ ደቀ መዝሙር በመሆኑ፥ ከነዚህ ታናናሾች ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ የሚሰጥ ሰው ዋጋውን አያጣም።”
ማቴዎስ 10:24-42 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ደቀመዝሙር ከመምህሩ፥ ባርያም ከጌታው አይበልጥም። ደቀመዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባርያም እንደ ጌታው ከሆነ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔልዜቡል ካሉት፥ ቤተሰቦቹንማ እንዴት ከዚህ የበለጠ አይሉአቸው? “እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና። በጨለማ የነገርሁአችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮአችሁ የሰማችሁትን በሰገነት ላይ ስበኩ። ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን እርሱን ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱ አንዲትዋ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተ ግን የራስ ጠጉራችሁ ሁሉ እንኳ ተቆጥሮአል። ስለዚህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ እናንተ ትበልጣላችሁ። ስለዚህ በሰዎች ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ። “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን በአባቱ ላይ፥ ሴት ልጅን በእናትዋ ላይ፥ ምራትን በአማትዋ ላይ ለማሥነሳት ነው፤ ለሰው ጠላቶቹ ቤተሰቦቹ ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔም ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። መስቀሉን ይዞ በኋላዬ የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኛት ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ግን ያገኛታል። “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይቀበላል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ይቀበላል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ በደቀ መዝሙር ስም ብቻ የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋውን አያጣም።”