በሕግ መሠረት፥ የመንጻት ሥርዓት የሚፈጸምበት ጊዜ ደረሰ፤ ስለዚህ ማርያምና ዮሴፍ ሕፃኑን በጌታ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ሄዱ። ይህንንም ያደረጉት በጌታ ሕግ “ወንድ የሆነ በኲር ልጅ ሁሉ ለጌታ ተሰጥቶ የተቀደሰ ይሆናል” የሚል ትእዛዝ ተጽፎ ስለ ነበር ነው። እንዲሁም በጌታ ሕግ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለመሥዋዕት ማቅረብ ይገባል” የሚል ትእዛዝ ነበረ። በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሰጠ ጻድቅ ሰው ነበር፤ የእስራኤልን የመዳን ተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበር። እርሱ የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። በዚያን ቀን መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ዮሴፍና ማርያምም በሕጉ መሠረት የተለመደውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ በገቡ ጊዜ ስምዖን ሕፃኑን ተቀብሎ ዐቅፎ፥ እግዚአብሔርን በማመስገን እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ የሰጠኸኝ የተስፋ ቃል ተፈጸመ፤ እንግዲህ አሁን እኔን አገልጋይህን በሰላም አሰናብተኝ፤ ማዳንህን በዐይኔ አይቻለሁ፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤ እርሱ ለአሕዛብ እውነትን የሚገልጥ ብርሃን ይሆናል፤ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” ዮሴፍና ማርያም ስለ ሕፃኑ በተባለው ነገር ሁሉ ይደነቁ ነበር። ስምዖን ከባረካቸው በኋላ በተለይ የሕፃኑን እናት ማርያምን እንዲህ አላት፦ “እነሆ! ይህ ሕፃን በእስራኤል ውስጥ ለብዙዎቹ የመጥፋት፥ ለብዙዎቹ ግን የመዳን ምክንያት ይሆናል፤ እርሱም ብዙዎች የማይቀበሉት ምልክት ይሆናል። በዚህም በብዙዎች ልብ ያለው ስውር ሐሳብ ይገለጣል፤ የአንቺንም ልብ የሐዘን ሰይፍ ሰንጥቆት ያልፋል።” እንዲሁም በዚያን ጊዜ ከአሴር ነገድ የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች። በዕድሜዋም በጣም የገፋች ሴት ነበረች፤ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ከተቀመጠች በኋላ ባልዋ ሞተባት፤ ከዚህም በኋላ ዕድሜዋ ሰማኒያ አራት ዓመት እስኪሆን ድረስ ከቤተ መቅደስ ሳትለይ በጾምና በጸሎት ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ታገለግል ነበር። በዚያኑ ጊዜ እርስዋም መጥታ ጌታን ታመሰግን ጀመር፤ ስለ ሕፃኑም የኢየሩሳሌምን መዳን በተስፋ ለሚጠባበቁ ሁሉ ትናገር ነበር። በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሥርዓት ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ መኖሪያ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብም የተሞላ ሆነ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ ከእርሱ ጋር ነበረ።
የሉቃስ ወንጌል 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 2:22-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos