የሉቃስ ወንጌል 2
2
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
(ማቴ. 1፥18-25)
1በዚያን ጊዜ በሮማውያን ግዛት ያሉ ሰዎች ሁሉ እንዲቈጠሩ ከሮማው ንጉሠ ነገሥት አውግስጦስ ታወጀ። 2ይህም የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ በተደረገ ጊዜ ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ ነበር። 3ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ስሙን ለማስመዝገብ ወደ ትውልድ አገሩ ይሄድ ነበር።
4ዮሴፍም በትውልዱ የዳዊት ዘር ስለ ነበረ በገሊላ ምድር ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ በይሁዳ ምድር ወደምትገኘው ወደ ዳዊት ከተማ፥ ወደ ቤተልሔም ሄደ፤ 5ሊመዘገብ የሄደውም ፀንሳ ከነበረችው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ነበር። 6በቤተልሔም ከተማ ሳሉ ማርያም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ። 7በዚያም የበኲር ልጅዋን ወለደች፤ በመታቀፊያ ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በበረት በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ አስተኛችው።
እረኞችና መላእክት
8በዚያም አካባቢ፥ በሜዳ ላይ ሌሊት መንጋቸውን እየጠበቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። 9እነሆ፥ ለእነርሱ የጌታ መልአክ ታያቸው፤ የጌታም የክብር ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ እነርሱም በጣም ፈሩ፤ 10መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ! ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን መልካም ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ፤ 11እነሆ! ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። 12ምልክቱም ይህ ነው፤ በመታቀፊያ ጨርቅ የተጠቀለለ ሕፃን በበረት ውስጥ በግርግም ላይ ተኝቶ ታገኛላችሁ።”
13በድንገት ብዙ የሰማይ መላእክት ከመልአኩ ጋር አብረው ታዩ፤ እግዚአብሔርንም በማመስገን፥
14“በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን!
በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን!” ይሉ ነበር።
15መላእክቱ ተለይተዋቸው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ ወደ ቤተልሔም እንሂድ፤ አሁን የተፈጸመውንና ጌታ የገለጠልንን ነገር እንይ” ተባባሉ።
16በፍጥነት ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኙ፤ ሕፃኑንም በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ ተኝቶ አዩት። 17ሕፃኑንም ካዩ በኋላ መልአኩ ስለ እርሱ የነገራቸውን አወሩ። 18ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ ባወሩላቸው ነገር ተደነቁ። 19ማርያም ግን፥ ይህን ሁሉ ነገር በልብዋ ይዛ ታሰላስለው ነበር። 20እረኞቹ፥ ሁሉ ነገር መልአኩ እንዳላቸው ሆኖ በማየታቸውና በመስማታቸው፥ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ፥ ወደ ስፍራቸው ተመለሱ።
የሕፃን ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ መወሰድ
21ከስምንት ቀን በኋላ ሕፃኑ በሚገረዝበት ሥነ ሥርዓት ላይ፥ ስሙ “ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ። ይህም ገና ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ያወጣለት ስም ነው። #ዘሌ. 12፥3፤ ሉቃ. 1፥31።
22በሕግ መሠረት፥ የመንጻት ሥርዓት የሚፈጸምበት ጊዜ ደረሰ፤ ስለዚህ ማርያምና ዮሴፍ ሕፃኑን በጌታ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ሄዱ። #ዘሌ. 12፥6-8። 23ይህንንም ያደረጉት በጌታ ሕግ “ወንድ የሆነ በኲር ልጅ ሁሉ ለጌታ ተሰጥቶ የተቀደሰ ይሆናል” የሚል ትእዛዝ ተጽፎ ስለ ነበር ነው። #ዘፀ. 13፥2፤12። 24እንዲሁም በጌታ ሕግ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለመሥዋዕት ማቅረብ ይገባል” የሚል ትእዛዝ ነበረ።
25በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሰጠ ጻድቅ ሰው ነበር፤ የእስራኤልን የመዳን ተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበር። 26እርሱ የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። 27በዚያን ቀን መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ዮሴፍና ማርያምም በሕጉ መሠረት የተለመደውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ በገቡ ጊዜ 28ስምዖን ሕፃኑን ተቀብሎ ዐቅፎ፥ እግዚአብሔርን በማመስገን እንዲህ አለ፤
29“ጌታ ሆይ! እነሆ፥ የሰጠኸኝ የተስፋ ቃል ተፈጸመ፤
እንግዲህ አሁን እኔን አገልጋይህን በሰላም አሰናብተኝ፤
30ማዳንህን በዐይኔ አይቻለሁ፤
31እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤
32እርሱ ለአሕዛብ እውነትን የሚገልጥ ብርሃን ይሆናል፤
ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።”
33ዮሴፍና ማርያም ስለ ሕፃኑ በተባለው ነገር ሁሉ ይደነቁ ነበር። 34ስምዖን ከባረካቸው በኋላ በተለይ የሕፃኑን እናት ማርያምን እንዲህ አላት፦ “እነሆ! ይህ ሕፃን በእስራኤል ውስጥ ለብዙዎቹ የመጥፋት፥ ለብዙዎቹ ግን የመዳን ምክንያት ይሆናል፤ እርሱም ብዙዎች የማይቀበሉት ምልክት ይሆናል። 35በዚህም በብዙዎች ልብ ያለው ስውር ሐሳብ ይገለጣል፤ የአንቺንም ልብ የሐዘን ሰይፍ ሰንጥቆት ያልፋል።”
36እንዲሁም በዚያን ጊዜ ከአሴር ነገድ የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች። በዕድሜዋም በጣም የገፋች ሴት ነበረች፤ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ከተቀመጠች በኋላ ባልዋ ሞተባት፤ 37ከዚህም በኋላ ዕድሜዋ ሰማኒያ አራት ዓመት እስኪሆን ድረስ ከቤተ መቅደስ ሳትለይ በጾምና በጸሎት ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ታገለግል ነበር። 38በዚያኑ ጊዜ እርስዋም መጥታ ጌታን ታመሰግን ጀመር፤ ስለ ሕፃኑም የኢየሩሳሌምን መዳን በተስፋ ለሚጠባበቁ ሁሉ ትናገር ነበር።
ወደ ናዝሬት መመለሳቸው
39በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሥርዓት ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ መኖሪያ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። #ማቴ. 2፥23። 40ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብም የተሞላ ሆነ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ ከእርሱ ጋር ነበረ።
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ
41ዮሴፍና ማርያም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። #ዘፀ. 12፥1-27፤ ዘዳ. 16፥1-8። 42ኢየሱስ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነውም ጊዜ እንደ ተለመደው በዓሉን ለማክበር ሄዱ። 43በዓሉ ከተፈጸመ በኋላ እነርሱ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ዮሴፍና ማርያም ግን እዚያ መቅረቱን አላወቁም ነበር። 44ከመንገደኞች ጋር አብሮ የሚሄድ መስሎአቸው የአንድ ቀን መንገድ ሲጓዙ ዋሉ፤ ከዚያም በኋላ ከዘመዶቻቸውና ከሚያውቋቸው ሰዎች ዘንድ ይፈልጉት ጀመር። 45ነገር ግን ሊያገኙት ስላልቻሉ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 46ከሦስት ቀንም በኋላ በቤተ መቅደስ አገኙት፤ በዚያም በሊቃውንት መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄም ሲያቀርብላቸው ነበር። 47የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይገረሙ ነበር። 48ዮሴፍና ማርያም በቤተ መቅደስ ባዩት ጊዜ ተደነቁ፤ በዚያን ጊዜ እናቱ፥ “ልጄ ምነው እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።
49ኢየሱስም “ስለምን ፈለጋችሁኝ? እኔ በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም ኖሮአልን?” አላቸው። 50እነርሱ ግን እርሱ የተናገረውን አላስተዋሉም።
51ከዚያም በኋላ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ወደ ናዝሬት ሄደ፤ ይታዘዛቸውም ነበር፤ እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልብዋ ትይዘው ነበር። 52ኢየሱስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት የተወደደ ሆኖ፥ በጥበብና በቁመት እያደገ ይሄድ ነበር። #1ሳሙ. 2፥26፤ ምሳ. 3፥4።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997