የሉቃስ ወንጌል 11:1-28

የሉቃስ ወንጌል 11:1-28 አማ05

አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም ባበቃ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው፥ አንተም እኛን መጸለይ አስተምረን!” አለው። ኢየሱስም “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ አላቸው፤ ‘[በሰማይ የምትኖር] አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ! መንግሥትህ ትምጣ! የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን! እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥ በደላችንን ይቅር በልልን፤ ወደ ፈተናም አታግባን’ [ከክፉ አድነን እንጂ።]” ቀጥሎም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ለምሳሌ ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ኖሮት፥ ያ ወዳጁ በእኩለ ሌሊት ወደዚያ ወደ ወዳጁ ቤት ሄዶ፥ ‘ወዳጄ ሆይ፥ እባክህ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ ወዳጄ የሆነ አንድ ሰው ከሩቅ መንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ምግብ የለኝም!’ ቢለው ታዲያ፥ ያ ወዳጁ ከውስጥ ሆኖ፥ ‘እባክህ አታስቸግረኝ! በሩ ተቈልፎአል፤ ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ተኝተዋል፤ ስለዚህ ተነሥቼ የፈለግኸውን እንጀራ ልሰጥህ አልችልም፤’ ይለዋልን? ምንም እንኳ ስለ ወዳጅነቱ ተነሥቶ ሊሰጠው ባይፈልግ ስለ ነዘነዘው ተነሥቶ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል እላችኋለሁ። “ስለዚህ እኔም እናንተን የምላችሁ ይህን ነው፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ መዝጊያ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። ከእናንተስ አባት ሆኖ፥ ልጁ [ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማን ነው?] ዓሣስ ቢለምነው በዓሣ ፈንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ ዕንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠትን ካወቃችሁ በሰማይ የሚኖር አባታችሁማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!” አንድ ቀን ኢየሱስ የማያናግር ጋኔን ከአንድ ድዳ ሰው ያስወጣ ነበር፤ ጋኔኑም በወጣ ጊዜ ድዳው ሰው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም በዚህ ነገር እጅግ ተደነቁ። አንዳንዶች ግን “አጋንንትን የሚያስወጣው የአጋንንት አለቃ በሆነው በብዔልዜቡል ነው፤” አሉ። ሌሎች ደግሞ ሊፈትኑት ፈልገው ከሰማይ አንድ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በርስ የሚለያይ ከሆነ፥ ያ መንግሥት ይጠፋል፤ እንዲሁም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ይወድቃል። ስለዚህ ሰይጣን እርስ በርሱ የሚለያይ ከሆነ የእርሱ መንግሥት እንዴት ጸንቶ መቆም ይችላል? እናንተ ግን ‘እርሱ አጋንንትን የሚያስወጣ በብዔልዜቡል ነው፤’ ትሉኛላችሁ። ታዲያ፥ እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል የማስወጣ ከሆንኩ ልጆቻችሁስ በማን ያስወጡአቸዋል? ስለዚህ የገዛ ልጆቻችሁ እንኳ ይፈርዱባችኋል። እንግዲህ እኔ አጋንንትን በእግዚአብሔር ኀይል የማስወጣ ከሆነ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መምጣትዋን ዕወቁ። “አንድ ኀይለኛ ሰው የጦር መሣሪያ ይዞ ቤቱን የሚጠብቅ ከሆነ ንብረቱ በደንብ ይጠበቅለታል፤ ነገር ግን ከእርሱ የበለጠ ኀይለኛ ሰው መጥቶ ካሸነፈው የተማመነበትን የጦር መሣሪያ ይወስድበታል ንብረቱንም ሁሉ ዘርፎ ያካፍላል። “ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ እኔን ይቃወማል፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ውስጥ በወጣ ጊዜ የሚያርፍበት ቦታ በመፈለግ ውሃ በሌለበት በደረቅ ምድር ሁሉ ይዞራል፤ የሚያርፍበት ቦታ ካላገኘ ግን ‘ወደወጣሁበት ቤቴ ተመልሼ ልሂድ’ ይላል። ተመልሶ ሲመጣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚህ በኋላ ሄዶ ከእርሱ ይብስ የከፉ ሌሎች ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል፤ ቀድሞ እርሱ በነበረበት ቤትም ገብተው በዚያ ይኖራሉ፤ የዚያም ሰው የመጨረሻ ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ የባሰ ይሆናል።” ኢየሱስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ አንዲት ሴት ከሕዝቡ መካከል ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “አንተን ወልዳ ያጠባች እናት የተባረከች ናት፤” አለች። ኢየሱስ ግን “የተባረኩስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በሥራ ላይ የሚያውሉት ናቸው፤” አላት።