አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም እንደ ጨረሰ፣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “ጌታ ሆይ፤ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው አንተም መጸለይን አስተምረን” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፤ “ ‘አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ የዕለት እንጀራችንን በየዕለቱ ስጠን፤ በደላችንን ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና። ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉው አድነን እንጂ።’ ” ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ቢኖረውና በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ፣ ‘ወዳጄ ሆይ፤ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ አንድ ባልንጀራዬ ከመንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ነገር የለኝምና’ ብሎ ለመነው እንበል። በቤት ውስጥ ያለውም፣ ‘አታስቸግረኝ፤ በሩ ተቈልፏል፤ ልጆቼም ዐብረውኝ ተኝተዋል፤ ከእንግዲህ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም’ ይለዋልን? እላችኋለሁ፤ ወዳጁ በመሆኑ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፣ ስለ ንዝነዛው ብቻ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል። “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። “ከእናንተ መካከል አባት ሆኖ ሳለ ልጁ ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጠው ይኖራልን? ወይስ ዕንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ በሰማይ ያለው አባት ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ?” አንድ ቀን ኢየሱስ ድዳ ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣለት በኋላ ድዳው ሰው ተናገረ፤ ሕዝቡም ተገረመ። አንዳንዶቹ ግን፣ “በአጋንንት አለቃ፣ በብዔልዜቡል፣ አጋንንትን ያወጣል” አሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሊፈታተኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳይ ከርሱ ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ የሚለያይ ቤትም ይወድቃል። ሰይጣንም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ፣ መንግሥቱ እንዴት ይጸናል? አጋንንትን በብዔልዜቡል እንደማወጣ ትናገራላችሁና። እንግዲህ እኔ አጋንንትን የማወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በማን ያወጧቸው ይሆን? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን አጋንንትን የማወጣው በእግዚአብሔር ጣት ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ መጣች ዕወቁ። “ብርቱ ሰው በሚገባ ታጥቆ ቤቱን ከጠበቀ፣ ንብረቱ በሰላም ይቀመጣል። ነገር ግን ይበልጥ ብርቱ የሆነ ሰው መጥቶ ካጠቃውና ካሸነፈው ታምኖበት የነበረውን ትጥቁን ያስፈታዋል፤ ምርኮውንም ወስዶ ለሌሎች ያካፍላል። “ከእኔ ጋራ ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋራ የማይሰበስብ ይበትናል። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ፣ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ ሳያገኝም ሲቀር፣ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም በኋላ ሄዶ ሌሎች ከርሱ የከፉ ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውበትም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታ የከፋ ይሆንበታል።” ኢየሱስ ይህን እየተናገረ እያለ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፣ “የተሸከመችህ ማሕፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው” አለችው። እርሱ ግን፣ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ።
ሉቃስ 11 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 11:1-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች