ኦሪት ዘሌዋውያን 16:15-34

ኦሪት ዘሌዋውያን 16:15-34 አማ05

ከዚህም በኋላ ለሕዝቡ የኃጢአት ማስተስረያ የሆነውን ፍየል ይረድ፤ ደሙንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አስገብቶ በኰርማው ደም ባደረገው ዐይነት፥ በስርየት መክደኛው ላይ፥ እንዲሁም በኪዳኑ ታቦት ፊት ይርጨው። በዚህም ዐይነት ቅድስተ ቅዱሳኑን ከእስራኤል ሕዝብ ርኲሰትና ከኃጢአታቸውም ሁሉ ለማጥራት የማንጻትን ሥርዓት ይፈጽማል፤ ንጹሕ ባልሆነ ሰፈር መካከል ስለሚገኝ ድንኳኑንም ለማንጻት እንዲሁ ያደርጋል። አሮን ለማስተሰረይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተሰቡ፥ ለእስራኤል ጉባኤ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ ድንኳን ውስጥ ማንም አይኑር፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ወዳለው መሠዊያ ወጥቶ መሠዊያውን ያንጻው፤ ከኰርማውና ከፍየሉ ጥቂት ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ጒጦች ይቀባ፤ ከደሙም ጥቂቱን ወስዶ በጣቱ እየነከረ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ይርጭ፤ በዚህም ዐይነት ከእስራኤል ሕዝብ ርኲሰትን በማንጻት መሠዊያውን የተቀደሰ ያደርገዋል። አሮን ቅድስተ ቅዱሳኑን፥ የመገናኛውን ድንኳን የቀረውን ክፍልና መሠዊያውንም የማንጻት ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ ለዐዛዜል የተመረጠውን ፍየል ወስዶ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። ሁለት እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ ይጭናል፤ የሕዝቡን ክፋት፥ ኃጢአትና ዐመፅ ሁሉ በመናዘዝ አዛውሮ በፍየሉ ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ ከዚህ በኋላ ለዚህ ሥራ የተመደበ ሰው ፍየሉን ነድቶ ወደ በረሓ ይወስደዋል። ፍየሉንም ኃጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ምንም ሰው ወደማይኖርበት ምድረ በዳ ወስዶ ይለቀዋል። “አሮንም ወደ ድንኳኑ ይግባ፤ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከመግባቱ በፊት ለብሶት የነበረውን የክህነት ልብስ አውልቆ፥ በዚያ ይተወው፤ በተቀደሰውም ቦታ ሰውነቱን ታጥቦ የዘወትር ልብሱን ይልበስ፤ ከዚያም ወጥቶ የራሱንና የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቅርብ። ኃጢአትን ለማስተስረይ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውንም የእንስሳ ስብ፥ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ የተመረጠውን ፍየል እየነዳ ወደ በረሓ ይዞት ሄዶ የነበረውም ሰው ወደ ሰፈር ከመግባቱ በፊት ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ። ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትና ኃጢአትን ለማስተስረይ ደማቸው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ የነበረው ኰርማና ፍየልም ከሰፈር ወደ ውጪ ተወስደው በእሳት ይቃጠሉ፤ እንዲሁም ቆዳቸው፥ ሥጋቸውና የሆድ ዕቃቸው በሙሉ ይቃጠል። እነርሱንም የሚያቃጥለው ሰው ወደ ሰፈር ከመመለሱ በፊት ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ። “ከዚህ የሚከተሉትን መመሪያዎች በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ቋሚ ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁአቸዋላችሁ፦ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እስራኤላውያንና በእነርሱ መካከል የሚኖሩ መጻተኞች ራሳቸውን ማዋረድ አለባቸው፤ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሥሩበት። በዚያን ዕለት ንጹሖች እንድትሆኑ የኃጢአት ማስተስረይ ይደረግላችኋል፤ ከዚያም ከኃጢአታችሁ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የነጻችሁ ትሆናላችሁ፤ ያም ዕለት እንደ ሰንበት የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ፤ በዚያን ቀን ራሳችሁን አዋርዱ ይህም የዘለዓለም ሥርዓት ነው። በአባቱ ምትክ ሊቀ ካህናት እንዲሆን ተለይቶ የሚሾመው ካህን የተቀደሰ የክህነት በፍታ ልብሱን ለብሶ ያስተሰርያል። እርሱም ለቅድስተ ቅዱሳኑ፥ ለመገናኛው ድንኳን፥ ለመሠዊያው፥ ለካህናቱና ለጉባኤው ያስተሰርያል። በዓመት አንድ ጊዜ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ሁሉ ማስተስረይ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል።” በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።